የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በዚህ ሳምንት ሱዳንን ይጎበኛሉ ተባለ
ሱዳን በወታደራዊ እና በሲቪል አመራሩ የሰፋ ልዩነት ምክንያት በፖለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች
ጄፍሪ ፌልትማን ሱዳንን የሚጎበኙት በሲቪሊያን የስልጣን ሽግግር ሂደት ላይ ከሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ለመምከር ነው
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በዚህ ሳምንት ወደ ሱዳን ይመጣሉ ተባለ፡፡
ፌልትማን እንደተባለው ወደ ካርቱም የሚመጡ ከሆነ በአንድ ወር ውስጥ ሁለተኛ የሱዳን ጉብኝታቸው ነው የሚሆነው፡፡
ልዩ መልዕከተኛው ወደ ካርቱም የሚመጡት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራውን የሱዳን የሲቪል መንግስት ለመደገፍ ነው፡፡
“ሱዳን የመከፋፈል አደጋ ተጋርጦባታል፤ እውነታው ይህ ነው” - አብደላ ሃምዶክ
የአል በሽርን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ በሽግግር ሂደት ላይ ያለችው ሱዳን በሲቪልና ወታራዊ የሽግግሩ አመራሮች ፍጥጫ ውስጥ ትገኛለች፡፡
በሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሃገሪቱ ጦር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከሚመራው የሲቪል አስተዳደር ጋር በሰፋ ልዩነት ውስጥ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡
በተለይ በቅርቡ ከተፈጸመውና ጦሩ አከሸፍኩት ካለው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ ልዩነቱ እንደሰፋ ነው የሚነገረው፡፡
ይህ ምናልባትም በከፍተኛ መስዋዕትነት የመጣውን ለውጥ ከግብ ሳይደርስ ሊያስተጓጉለው እንደሚችል ስጋታቸውን የገለጹ በርካታ ሱዳናውያን ድርጊቱን በመቃወም ከሰሞኑ ወደ አደባባዮች ወጥተው ነበር፡፡
የሱዳን መንግስትን የሚቃወሙ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ካርቱም አደባባይ ወጡ
ልዩነቱን በማጥበብ ሲቪሊያን መንግስትን የማቋቋሙ ኃላፊነትም ሃገራቸው ቅርቃር ውስጥ መውደቋን ደጋግመው ባስታወቁት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ላይ ወድቋል፡፡
በዚህ ምክንያትም ልዩ መልዕክተኛዋን መላልሳ ወደ ሱዳን የላከችው አሜሪካ ሃምዶክን መደገፍ እንደምትፈልግ ከአሁን ቀደምም አስታውቃለች፡፡
የአምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ምክትል ሆነው በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ልዩ መልዕክተኛነት እያገለገሉ የሚገኙት ፔይቶን ኖፕፍ ቀድመው ገብተው ካርቱም ነው የሚገኙት፡፡
ፌልትማንም በተያዘው ሳምንት ቀሪ ቀናት ወደ ሱዳን እንደሚያቀኑ ይጠበቃል፡፡
ልዩ መልዕክተኛው ከአሁን ቀደም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው፡፡