አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ዜጎቻቸው በአስቸኳይ ሊባስኖስን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ
አሜሪካ ዜጎቿ ባገኙት ትኬት ሊባኖስን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ አሳስባለች
ኢራን በሃማስና በሄዝቦላ አመራሮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ እንደምትበቀል መዛቷን ተከትሎ ስጋት ነግሷል
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሀገራት ዜጎቻቸው በአስቸኳይ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ መስጠታቸው ተሰምቷል።
እስራኤል በሰዓታት ልዩነት ውስጥ የሃመስ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ እና የሄዝቦላህ የጦር መሪ ፉአድ ችኩርን መግደሏን ተከትሎ፤ ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
የኢራንን ዛቻ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋት መንገሱም ተነግሯል።
ይህንን ተከትሎም አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ብሪተኒያ እና ካናዳን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሀገራት ዜጎቻው በአስቸኳይ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰባቸው ተሰምቷል።
በቤሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፤ የአሜሪካ ዜጎች በተገኘው በማንኛውም የበረራ ቲኬት በአስቸኳይ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ ያሳሰበ ሲሆን፤ ለቀው ለማይወጡ ደግሞ ለረጅም ጊዜ እቅድ እንዲያዘጋጁ እና መጠለያ ምሽግ ቦታ እንዲሆኑ አሳስቧል።
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም የሀገሪቱ ዜጎች የንግድ በረራዎች ከመቋረጣቸው በፊት በአስቸኳይ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል።
ፈረንሳይም ዜጎቿ ወደ ሊባኖስ እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ ያወጣች ሲሆን፤ ሊባኖስ ያሉ ዜጎቿም ወደ ፈረንሳይ የሚደረጉ በረራዎች ስላልቆሙ በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አሳስባለች
ካናዳ በበኩሏ ዜጎቿ ወደ እስራኤል ከመጓዝ እንዲቆጡ ያሳሰበች ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ነው።
ከሰሞኑ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የጦርነት ስጋት እየተባሰ መምጣቱን ተከትሎ ግዙፍ የዓለማች አየር መንገዶች ወደ እስራኤል፣ ሊባኖስ እና ኢራን የሚያደርጉትን በረራ አቁመዋል።
ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ለይ ኢራን በእስራኤል ላይ የከፈተችውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከትሎ በርካታ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት አየር መንዶች የመካከለኛው ምስራቅ የአየር ክልችን መጠቀም መቆማቸው ይታወሳል።
በሰዓታት ልዩነት ውስጥ የሂዝቦላ እና የሀማስ ከፍተኛ አመራሮች ግድያን ተከትሎ ሊኖር የሚችለው የአጸፋ ምላሽ ቀጠናዊ ግጭትን ሊቀሰቀስ እንደሚችል ተሰግቷል።
ኢራን የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህ በዋና ከተማዋ ቴህራን በተፈጸመባቸው የሚሳኤል ጥቃት መገደላቸው ተከትሎ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች፡፡
ይህን ተከትሎ እስራኤልን ብቻዋን እንደማትተው ያስታወቀችው አሜሪካ የእስራልን ጦር ለመርዳት በሚል የጦር መርከቦቿን እና ተዋጊ ጄቶችን ወደ ስፍራው ማሰማራቷን አስታውቃለች፤ ብሪታንያም ወታደራዊ መርከቦቿን እና የአየር ኃይሏን በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አዛለች።
የተባሩት መንግስታ ጸጥታው ምክር ቤት የአመራሮቹን ግድያ ተከትሎ ሂዝቦላ እና ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃት የሚሰነዝሩ ከሆነ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንደሚሆኑ እና መጠነ ሰፊ ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡