ኢትዮጵያ ከታይላንድ እና ማይናማር ጋር የስራ ስምምነት እንደሌላት አስታወቀች
ኢትዮጵያዊያን ለስራ በሚል ወደ ታይላንድ እና ማይናማር እንዳይጓዙ ውጭ ጉዳይ አሳስቧል
የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑን ሚንስቴሩ አስታውቋል
ኢትዮጵያ ከታይላንድ እና ማይናማር ጋር የስራ ስምምነት እንደሌላት አስታወቀች።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወደ እስያዎቹ ታይላንድ እና ማይናማር በህገወጥ ደላሎች እየተታለሉ እየተጓዙ መሆኑን ተናግረዋል ።
ኢትዮጵያዊያኑ ለስራ በሚል ወደ ሁለቱ ሀገራት እየተጓዙ መሆኑን አውቀናል ያሉት አምባሳደር ነብዩ ይሁንና ኢትዮጵያ ከተባሉት ሀገራት ጋር የስራ ስምምነት እንዳልተፈራረመች ተናግረዋል።
በህገወጥ ደላሎች ተታለው ወደ ስፍራው የሄዱ እና በጉዳት ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳትም በቶኪዮ እና ኒው ዴልሒ ባሉ ኢምባሲዎች በኩል ጥረቶች በመደረግ ላይ እንደሆነ አምባሳደር ነብዩ ገልጸዋል።
አምባሳደር ነብዩ በመግለጫቸው ላይ ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ጉዳይ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ ነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ እገዳ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ የተፈጠረው ክስተት በተቋማት መካከል ያለ እና በውይይት ሊፈታ የሚችል መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ከሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡበትን አለመግባባት ለመፍታት ምን እያደረጉ ነው? በሚልም ጋዜጠኞች ለቃል አቀባዩ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ነው።
አምባሳደር ነብዩ በምላሻቸው " ሁለቱ ሀገራት ከአንድ ወር በኋላ በቱርክ አንካራ ሊያካሂዱት ያሰቡት የሁለተኛው ድርድር እንደሚካሄድ እንጠብቃለን" ብለዋል።
"ይሁንና ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እስከ ህይወት መስዋዕትነት የደረሰ አበርክቶ ቢኖራትም የተወሰኑ አመራሮች ይህን ታሳቢ ያላደረጉ ሀሳቦችን በተለያዩ መንገዶች እያንጸባረቁ ነው" ሲሉም አምባሳደር ነብዩ ገልጸዋል።
የሶማሊያ አንዳንድ አመራሮች በኢትዮጵያ ላይ ያልተገቡ አስተያየቶችን ቢሰጡም ለመልካም ጉርብትና በሚል በሚሰጡ ያልተገቡ መግለጫዎችን ትዕግሥት የተሞላበት እንዲሆን በሚል ኢትዮጵያ ለመሪዎቹ አስተያየት ምላሽ እንዳልሰጠችም ተናግረዋል።