ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃን በፍትሃዊና ምክንያታዊ የመጠቀም ምሳሌ እንደሚሆን ተገልጿል
ኢትዮጵያ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሰፍን አሳሰበች።
በአፍሪካ የውሃ ሀብትን በእኩልነት እና በምክንያታዊነት መጠቀም ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሁለተኛው አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የአፍሪካ ውሃ ሀብት ለአፍሪካ ብልጽግና በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው በዚህ ጉባኤ ላይ የውሃ ሀብት ጥናት ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች እና መሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ደመቀ መኮንን በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሰፍን አሳስበዋል፡፡
የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር እና ሀብትን በበላይነት ለመቆጣጠር መፈለግ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀምን ለማረጋገጥ ዋነኛ እንቅፋት መሆኑንም አቶ ደመቀ በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድንበር ተሸጋሪ የውሃ ሀብቶችን በፍትሃዊነት መጠቀም እንዲቻል ስትጥር መቆየቷን የተናገሩት አቶ ደመቀ ተጨማሪ ጥረቶች ሌሎች ሀገራትም እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃን በፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ከመጠቀም አንጻር ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆንም አቶ ደመቀ አክለዋል፡፡
በሁለት ተርባይኖቹ ሀይል ማመንጨት የጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ከ84 በመቶ በላይ ተጠናቋል መባሉ ይታወሳል፡፡
በያዝነው ክረምት ወራት ውስጥ ተጨማሪ ውሃ እንደሚይዝ የሚጠበቀው ይህ ግድብ ውሃው የሚያርፍበት ስፍራ ጥርጊያው ሲካሄድ ቆይቷል ተብሏል፡፡