“የትግራይ ክልል አትሌቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሊገናኙ በመሆኑ ደስታዬ ወደር የለውም”- አትሌት ደራርቱ
አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተመራና የትግራይ ክልል ተወላጅ አትሌቶችን የያዘ ቡድን ዛሬ ወደ መቀሌ አቅንቷል
ደራርቱ፤ “የእኔ ምኞት ትግራይን ጨምሮ መላ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላም እንዲሆን ነው” ብላለች
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተመራና የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ አትሌቶችን የያዘ የልዑካን ቡድን ዛሬ ረፋድ ወደ መቀሌ አቅንቷል፡፡
የጉዞው ዓላማ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ አትሌቶችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የልዑካን ቡድኑ የትግራይ ክልል ተዋላጅ የሆኑና በዓለም መድረክ በርካታ ስኬቶች ያስመዘገቡ ብርቅዬ አትሌቶች፣ ዘመድ አዝማድ እና የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ያካተተ ነው።
በጉዞው ከተሳተፉ የትግራይ ክልል ተወላጅ ከሆኑ አትሌቶች መካከል፤ በቶኪዮ ኦሎምፒክ እና በአሜሪካው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች የነበሩት ለተሰንበት ግደይ፣ ጎተይቶም ገብረ ስላሴ እና ጉዳፍ ጸጋይ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።
“የትግራይ ክልል ተወላጅ አትሌቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ” መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች በተለያዩ መድረኮች ስትጠይቅ የነበረችው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ አትሌቶችን ይዛ ወደ መቀሌ መጓዟ የፈጠረባት ደስታ እጅግ ላቅ ያለ እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግራለች
“የትግራይ አትሌቶች ከወላጆቻቸው ጋር ሊገናኙ መሆኑ እንደ አንድ እናት፣ በስፖርት አከባቢ ያለች አመራር እና ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ደስታዬ ወደር የለውም፤ ሰላሙ ያዝልቅልን እላለሁ” ብላለች።
“እየሆነ ያለው ነገር ሰላምን ዋጋ ምን ያህል ውድ እንደሆነ የሚያሳይ ነው” ያለችው አትሌት ደራርቱ፤ በከባድ ጫና ውስጥ ሆነው ለሀገራቸው በርካታ ስኬቶችን ስያስመዘግቡ ለነበሩ አትሌቶች ከቤሰተብ ጋር መገናኘት ትልቅ ደስታ የሚፈጥር መሆኑን መሆኑም ገልጻለች።
“እኔ አራት ኦሎምፒኮች ተሳትፌ ስመጣ ወንድሞቼና እና ሀሉም የስፖርት ወዳድ ማህበረሰብ እስከ ቤተመንግስት መጠጥተው የደስታው ተካፋይ ነበሩ፤ ያ! ለኔ ትልቅ ደስታ የሚሰጠኝ ነበር እናም የትግራይ አትሌቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸው ትልቅ ደስታ የሚፈጥርላቸው ይሆናል” ብላለች ደራርቱ።
ወደ መቄሌ የሚደረገው ጉዞ የአንድ ቀን ብቻ መሆኑን የገለጸችው አትሌት ደራርቱ፤ ልዑኩ በቆይታው ከክልሉ የስፖርት ቢሮ አመራሮች ጋር በመገናኘት በቀጣይ የትግራይ አትሌቶችን መልሶ ወደ ስፖርት ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ እንደሚመክርም አስታውቃለች።
አትሌት ደራርቱ መቀሌ ቆይታዋ ከትግራይ ባለስልጣናት ጋር የመገናኘት እቅድ ያላት እንደሆነ አል ዐይን አማርኛ ላቀረበላት ጥያቄም “እርግጠኛ ባልሆንም ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር ልንገኛኝ እንችል ይሆናል፤ዋና ዓላማችን ግን እዛ ሄደን አትሌቶቻችን ከቤተሰቦቻቸው እንዲገናኙ ማድረግ ነው” የሚል ምለሽ ሰጥታለች።
አትሌቶቹ ቤሰቦቻቸው ካገኙ በኋላ በሚቀጥሉት አምስት ስድስት ሳምንታት ለሚካሄደው የሀገር አቋራጭ ውድድር በጥሩ መንፈስ ልምምድ እንዲጀምሩ ማድረግ ነው የእኛ እቅድ ስትልም አክላለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፍላጎት የሆነውን የተደረሰው ስምምነት ከዚህም የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተማጽናለች።
“ትግራይን ጨምሮ መላ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላም እንዲሆን ነው የእኔ ምኞት፤ በእርግጠኝት የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትም ሆነ የፌደራል መንግስት ህዝባቸውን ለማካስ የሰላም ሁኔታ አጠናክረው ይቀጥላሉ ብየ አስባለሁ” ባላለች አትሌት ደራርቱ።
ሀገር ማስተዳደር ትልቅ ኃላፊነት የሚጠይቅ ነው ያለችው ደራርቱ አሁንም ለኢትዮጵያ የሚበጀው “በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገርና የሰላም መንገድ ብቻ ነው” ስትልም ተናግራለች።