በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ ከ1 ቢሊዮን በላይ ብር ያስፈልጋል ተባለ
በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች በቶሎ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ ከ29 ሚሊዮን በላይ ብር ወጪ መደረጉም ተገልጿል
በጦርነቱ ምክንያት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ማጣቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል
በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ ከ1 ቢሊዮን በላይ ብር ያስፈልጋል ተባለ፡፡
ላሊበላ፣ ሁመራ፣ ወልቃይት እና ሰቆጣ አካባቢዎች አሁንም ኤሌክትሪክ እያገኙ አይደለም ተብሏል።
በጦርነቱ ምክንያት 231 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሀይል እንደባከነበትም ተቋሙ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ባደረሰው ጉዳት ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
የተቋሙ የኮሙንኬሽን ሀላፊ አቶ ሞገስ መኮንን በመግለጫው ላይ እንዳሉት ህወሓት በከፈተው ጦርነቱ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ንብረት ዘረፋ እና ውድመት ደርሷል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቱን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ቁመና ለመመለስ 23 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ 1 ቢሊዮን በላይ ብር እንደሚያስፈልም አቶ ሞገስ ተናግረዋል ።
ህወሓት ወደ ሁለቱ ክልሎች በከፈተው ጦርነት በርካታ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ከመውደሙ ባለፈ 231 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሀይል ሳይሸጥ መባከኑንም አቶ ሞገስ አክለዋል።
የህወሓት ሀይል ከአፋር እና አማራ ክልሎች አብዛኛው ቦታዎች ተገዶ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ አብዛኛዎቹ ቦታዎች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ ቢቻልም አሁንም ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ አካባቢዎች እንዳሉም ተገልጿል።
በወልቃይት፣ በሁመራ፣ በላሊበላ እና በሰቆጣ አካባቢዎች እንዲሁም በአፋር ክልል ዞን ሁለት አሁንም ኤሌክትሪክ እያገኙ አይደለም ብለዋል አቶ ሞገስ።
ወልቃይት እና ሁመራን መሰል አካባቢዎች ኃይል በዋናነት በሽሬ መስመር ከትግራይ ያገኙ የነበረ መሆኑ የተቋረጠውን የኃይል አቅርቦት በቶሎ ለመመለስ እንዳላስቻለም ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡
በአፋር አሁንም ጦርነት ያለ መሆኑ በተመሳሳይ መልኩ የኃይል አቅርቦቱን በቶሎ ለመመለስ እንዳላስቻለም ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት 53 በመቶ ያህሉ በጦርነቱ መውደሙም ተገልጿል።