ክትባቱ በዛሬው እለት በአዲስ አበባና በክልሎች መሰጠት የጀመረ ሲሆን በቅድሚያ ለጤና ባለሙያዎች እየተሰጠ ነው
ኢትዮጵያ እስከ መጭው ታህሳስ 2014ዓ.ም ድረስ 20 በመቶ የሚሆነውን ህዝቧን ለመከተብ ማቀዷን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ክትባቱ በዛሬው እለት በፌደራል ደረጃ በአዲስ አበባና በክልሎች መሰጠት ተጀምሯል፡፡
በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ክባቱን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ክትባቱ መምጣት “ከፍተኛ ብስራት ቢሆንም ለሁሉም ማዳረስ ስለማይቻል” ቅድመ ጥንቃቄ ማድረጉ ሊዘነጋ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር 2.2 ሚሊዮን ክትባት በህንዱ ሴረም ኢኒስትቲዩት የተመረተ ክትባት ባለፈው ሳምንት መረከቧ ይታወሳል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጨመሩንና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የኮሮና ጽኑ ህሙማን ቁጥርም አሻቅቧል፡፡
በትናንትናው እለት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የበኮቪድ 19 የመያዝ ምጣኔ አስጊ በሆነ ደረጃ ላይ መደረሱን ገልጾ ነበር፡፡ ኢኒስቲትዩቱ መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያም በኮቪድ 19 ቫይረስ የመሰራጨት አቅሙን ጨምሮ አስጊ በሆነ ደረጃ በ12.80 በመቶ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ ጨምሯል፡፡
መጋቢት 1 እና 2፣ 2013ዓ.ም የወጡ ሪፖርቶችን ሲታዩ፡ 01/2013 በኢትዮጵያ 7 ሺህ 819 ግለሰቦች የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 543 ግለሰቦች የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መግባቱ የተረጋገጠው መጋቢት 4፣2012ዓ.ም ሲሆን በወቅቱም ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ከቡርኮና ፋሶ የመጣ ጃፓናዊ ዜጋ ላይ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን 2 214 180 ሰዎች ላይ የኮሮና ምርምራ የተደረገ ሲሆን ከእነኢህ ውስጥ 172 571 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ 2510 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡