የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ በትናንትናው እለት ባህርዳር ከተማ ገብቷል
ከ23 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባህር ዳር ከተማ ይካሄዳል።
ጨዋታው ከሰኔ 26 እስከ ሀምሌ 11 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑንም የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
በውድድሩ ላይ 11 የምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ሀገራት እና አንድ ተጋባዥ ሀገር በድምሩ 12 ሀገራት እንደሚካፈሉም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በውድድሩ ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ በትናንትናው እለት ባህርዳር ከተማ ገብቷል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አባላትን ፤ከሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለ35 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅት ላይ መቆታቸውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መጥቀሳቸው ይታወሳል።
“በተጫዋቾቹ ላይ ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት አይቼባቸዋለሁ እስከ አሁን ባየሁት ነገር ደስተኛ ነኝ” ብለዋል ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በመግለጫቸው።
በውድድሩ የሚሳተፉ የምሥራቅና መካከለኛው ቀጠና የአፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖችም በቅርብ ቀናት ባሕር ዳር ከተማ እንደሚገቡ መገለፁን ከአማራ አማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።