ኢትዮጵያ ነገ በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ በተሰናዳው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስብሰባ ላይ አትሳተፍም
ኢትዮጵያ ነገ በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ በተሰናዳው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስብሰባ ላይ አትሳተፍም
ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር በአሜሪካ ሊካሂድ የታሰበው ስብሰባ ላይ እንደማትገኝ አስታወቀች ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን መካከል በአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ ሴክሬተሪ እና የዓለም ባንክ ፕሪዝዳንት በታዛቢነት የተገኙበት የሶስትዮሽ ድርድር በአሜሪካ ሲካሂድ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አሁንም በአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ ሴክሬተሪ የተጠራው እና በዋሺንግተን ዲሲ የካቲት 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሂድ በታሰበው የሶስትዮሽ የድርድር መድረክ፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባላማጠናቀቁ፣ ኢትዮጵያ አልሳተፍም ብላለች፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ በአሜሪካ በመገኘት ውይይቱን ማድረግ እንዳልተቻለ ጥሪውን ላደረገው የአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ የኢትዮጵያ መንግስት ማስታወቁን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚ/ር ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የግብጹ አህራም ኦንላይን እንደዘገበው የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ በስብሰባው ለመታደም ወደ አሜሪካ አቅንተዋል፡፡ በአሁኑ ስብሰባ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበረም ነው አህራም በዘገባው የጠቆመው፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ትናንት የካቲት 17 ማምሻውን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ጣሊያን ማምራታቸው ይታወቃል፡፡ በነገው እለት በዋሺንግተን ዲ.ሲ. ይካሄዳል በተባለው የሶስትዮሽ ስብሰባ ላይ አቶ ገዱን ጨምሮ የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ ይጠበቅ ነበር፡፡