አብን የአማራ እና የኦሮሞ ፖለቲከኞች መቀራረብን ይደግፋል
በፖለቲካ ልሂቃኖች እና ድርጅቶች የሚደረገው ”ሃቀኛ“ ጥረት ኢትዮጵያን ለማዳን ይበጃል-ሊቀመንበሩ
ፎረም ለመመስረት የሚደረገው ጥረት ሊበረታታ የሚገባው ነው
አብን የአማራ እና የኦሮሞ ፖለቲከኞች መቀራረብን ይደግፋል
በአማራ እና ኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል መቀራረብን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ፡፡
ንቅናቄው ከሰሞኑ ያደረገውን መዋቅራዊ ማሻሻያ እና የአመራር መተካካት በማስመልከት አዲስ አበባ ግንፍሌ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥቷል፡፡
የአማራ እና ኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች ሊቀራረቡ የሚችሉበትን የጋራ ፎረም ለመፍጠር የሚያስችል ጥረት መጀመራቸው የሚበረታታ ነው ያሉት አዲሱ የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ (ረዳት ፕሮፌሰር) ለኢትዮጵያ እንደሚበጅ ተናግረዋል፡፡
በኃይሎቹ መካከል ልዩነት ቢኖርም ልዩነቱን ተገንዝቦ ሊያግባባ እና የጋራ ሊሆን በሚችል ጉዳይ ላይ መስራቱ የሚበረታታ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ አብን ጥረቱ እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት አለው ብለዋል፡፡
”ይህን በመገንዘብ ልሂቃኖች እና የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያደርጉት ሃቀኛ ጥረት“ ኢትዮጵያን ለማዳን እንደሚበጅም ነው የተናገሩት፡፡
”ከመነጋገርና ከመወያየት ውጭ አማራጩ መፍረስ በመሆኑና ሁላችንም ይህን ስለማንፈልግ“ በሚል ባስቀመጡት ንግግርም አብን ከአሁን ቀደም የተካሄዱ ሁለት ጉባዔዎች እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ፍላጎት አለው ብለዋል፡፡