ኮሮና በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች እንዲሁም በቬትናም ጦርነት ወቅት ከሞቱት በላይ በርካታ አሜሪካውያንን ገድሏል
ፕሬዝዳንት ባይደን ለሟቾቹ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ ከትናንት ሰኞ ጀምሮ እስከ ቀሪ የሳምንቱ ቀናት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አዘዋል
አሜሪካ በወረርሽኙ ምክንያት የሞቱ ግማሽ ሚሊዬን ዜጎቿን አስባለች
በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ግማሽ ሚሊዬን ሰዎች ትናንት ታስበው አምሽተዋል፡፡
መንበረ ስልጣኑን ተቆናጠው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከገቡ አንድ ወር ያስቆጠሩት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ከምክትላቸው ካማላ ሃሪስ ጋር በመሆን የቫይረሱን ሰለባዎች ሻማ በማብራት እና በሌሎችም ስነ ስርዓቶች አስበዋል፡፡
ከየትኛውም ሃገር በላይ በአሜሪካ የበርካታ ዜጎች ህይወት በቫይረሱ መነጠቁ ልብ የሚሰብር እንደሆነ ነው ባይደን የተናገሩት፡፡
በዚህም ከትናንት ሰኞ ጀምሮ እስከ ቀሪ የሳምንቱ ቀናት የሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ ለሟቾቹ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አዘዋል እንደ ዋሺንግተን ፖስት ዘገባ፡፡
ልክ የዛሬ ዓመት ወርሃ መጋቢት ላይ የሃገሪቱ የጤና ልሂቃን አሜሪ በጥብቅ የእንቅስቃሴ እገዳ ላይ እንኳን ሆና ከ240 ሺ የሚልቁ ዜጎቿል ልትነጠቅ እንደምትችል ገምተው ነበረ፡፡
ሆኖም በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ተገምቶ ከነበረው በላይ ነው፡፡
በ1ኛው እና በ2ኛው የዓለም ጦርነቶች እንዲሁም በቬትናም ጦርነት ወቅት ከሞቱ አሜሪካውያንን ቁጥር ይልቃል ሲሉም ነው እነ ኒውዮርክ ታይምስ የዘገቡት፡፡
ቫይረሱ በመላው ዓለም ከገደላቸው ሰዎች 20 በመቶ ያህሉን በምትይዘው አሜሪካ በአጠቃላይ ከ28 ሚሊዬን የሚልቁ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ምንም እንኳን የቫይረሱ የስርጭት መጠን እየቀነሰ የክትባቶች አቅርቦት እየጨመረ ቢሆንም መቼ ሊያበቃ እንደሚችል በውል የታወቀ ነገር አለመኖሩ ከፍተኛ ስጋትን ደቅኗል፡፡
በተለይም ቫይረሱ በአዳዲስ ዝርያዎች እያገረሸ ነው መባሉ ብዙዎችን ያሳሰበ ጉዳይ ነው፡፡