ዋሊያዎቹ ዛሬ ጥሎ ማለፉን መቀላቀላቸውን ወይ ከአፍሪካ ዋንጫ መሰናበታቸውን ያረጋግጣሉ
4 የግብ እዳ ኖሮባት ያለምንም ነጥብ በምድብ 1 በስተግርጌ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ ጨዋታውን ማሸነፍና የኬፕ ቨርዴን ውጤት መጠበቅ ግድ ይላታል
ዋሊያዎቹ ምሽት 1፡00 ላይ ከቡርኪና ፋሶ ጋር የመጨረሻ የምድብ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
ኢትዮጵያን ከቡርኪናፋሶ የሚያፋልመው የዛሬው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ከሚጠበቁ የዛሬ ጨዋታዎች መካል አንዱ ነው፡፡
ጨዋታው የምድብ ጨዋታዎችን ተሻግሮ 16 ብሔራዊ ቡድኖች የሚፋለሙበትን ጥሎ ማለፍ ማን እንደሚቀላቀል የሚለይበት ነው፡፡
ይህን እድል ለማግኘት ዋሊያዎቹ ዛሬ ምሽት 1፡00 ላይ ‘ዘ ስታሊዮንስ’ በሚል ቅጽል ስም ከሚታወቁት ቡርኪና ፋሷውያን ጋር በባፎሳም ኩዌ ኮንግ ስታዲየም ይጫወታል።
3ኛውና የመጨረሻው የምድብ ጨዋታ በሆነው በዚህ ፍልሚያ ኢትዮጵያ ለማሸነፍ ቡርኪና ፋሶ ደግሞ ላለመሸነፍ ነው የሚጫወቱት፡፡
ማሸነፍ ካልሆነም አቻ መውጣት፤ ያለምንም የግብ እዳ በ3 ነጥቦች ምድብ 1ን በሁለተኛነት እየመራች ያለችውን ቡርኪናፋሶን ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፋል፡፡ በእርግጥ አቻነቱ የኬፕ ቨርዴን ውጤት ከመጠበቅ የሚያስቀር አይደለም፡፡
ያለምንም ነጥብ በምድቡ በስተግርጌ የተቀመጠችውና አራት የግብ እዳ ያለባት ኢትዮጵያ ደግሞ ጨዋታውን ማሸነፍና የካሜሮንን እና የኬፕ ቨርዴን ውጤት መጠበቅ ግድ ይላታል፡፡
ኢትዮጵያ ቡርኪናፋሶን ብታሸንፍ እንኳ ያለ ምንም የግብ እዳ 3 ነጥብ የያዘችውን የኬፕ ቨርዴን ውጤት መጠበቋ የማይቀር ነው፡፡
የ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረችው ቡርኪናፋሶ በወቅቱ በሰውነት ቢሻው ይሰለጥን የነበረውን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን 4 ለ 0 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
ስለ ዛሬው ጨዋታ ወሳኝነት የተናገሩት የቡርኪና ፋሶው አሰልጣኝ ካሙ ማሎ በርትራንድ ትራዖሬ ከኮሮና አገግሞ መመለሱ ብዙ አማራጮችን የሚሰጠኝ ነው ብለዋል፤ ዋሊያዎቹን እንደማያቀሉ ነገር ግን ለማሸነፍ መቁረጣቸውን በመጠቆም፡፡
ከአሁን ቀደም ካደረግናቸው ሁለት ጠንካራ ጨዋታዎች ተምረናል ያሉት የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ዉበቱ አባተ በበኩላቸው ለጉብኝት አልመጣንም ስለሆነም የቻሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ለተጫዋቾቼ ነግሬያቸዋለሁ ብለዋል፡፡
የአጨዋወት ስልት ለውጥ ማድረጋቸውን የገለጹት አሰልጣኝ ውበቱ ለውጡ ለአሸናፊነት ሊያበቃቸው እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
በዛሬው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ የውድድሩ አዘጋጅ እና የምድብ 1 መሪ ካሜሩን በተመሳሳይ ሰዓት ከኬፕ ቨርዴ የምትፋለምም ይሆናል፡፡