የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ 130 አውሮፕላኖችን እንደሚገዛ ገለጸ
አየር መንገዱ ከሁለት ዓመት በኋላ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር 271 አደርሳለሁ ብሏል
ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ጉባኤ በቱርክ ኢስታምቡል በመካሄድ ላይ ነው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ 130 አውሮፕላኖችን እንደሚገዛ ገለጸ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈረንጆቹ 2035 ላይ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር 271 የማድረስ እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በቱርክ የኢኮኖሚ መዲና ኢስታምቡል እየተካሄደ ባለው የዓለም አቪዬሽን ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።
አቶ መስፍን ለአቪዬሽን ዴይሊ እንዳሉት አየር መንገዱ አሁን ላይ 140 አውሮፕሎኖች እንዳሉት ገልጸው ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን የማስፋት እቅድ እንዳለው ገልጸዋል።
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ ይዞ የናይጄሪያ አየር መንገድን ለማቋቋም ተስማማ
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማትን አሸነፈ
አየር መንገዱ የ2035 እቅዱን ለማሳካትም ተጨማሪ 130 አውሮፕላኖችን መግዛት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ለዚህ እቅዱም የቦይንግ እና ኤርባስ ምርቶችን በማመማተር ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን በዓመቱ መጨረሻ ግዢውን ለመፈጸም እንደሚያዙ አክለዋል።
አየር መንገዱ በዚህ ዓመት 29 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ያዘዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 17ቱ 737 ማክስ አውሮፕላን፣ አምስት 777 ማክስ አውሮፕላን፣ አንድ 787- እና ስድስት ኤ350-1000 ኤርባስ ከታዘዙት አውሮፕላኖች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
አየር መንገዱ በዚህ ዓመት ካዘዛቸው አውሮፕላኖች መካከልም 12ቱን እንደተረከበ የተገለጸ ሲሆን በኮሮና ቫይረስ ተቀዛቅዞ የቆየውን ዓለም አቀፍ በረራ በሙሉ አቅሙ እየተጠቀመ ነው ተብሏል።
እንደ አቶ መስፍን ገለጻ አየር መንገዱ በአፍሪካ ብቻ 63 የበረራ መዳረሻ ያለው ሲሆን በተያዘው ዓመት ለ13 ሚሊዮን ዜጎች የበረራ መስተንግዶ ሰጥቷል።
በቀጣይም ወደ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ደቡብ አሜሪካ እና ሰሜን አሜሪካ ከተሞች ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን ለማስፋት በጥረት ላይ መሆናቸውን ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።