በአየር መንገዱን ለ 37 ዓመታት አገልግለዋል
ላለፉት 11 ዓመታት ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ተወልደ ገ/ማሪያም ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸው ተገለጸ፡፡
አቶ ተወልደ ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ለተቋሙ ሰራተኞች በኢሜል ማሳወቃቸውን አል ዐይን አማርኛ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከኃላፊነታቸው የለቀቁት ከጤና ጋር በተገናኘ መሆኑም ተገልጿል፡፡
አቶ ተወልደ ህክምናቸውን በአሜሪካ እየተከታተሉ ሲሆን ወደ አሜሪካ ያቀኑትም ከግማሽ ዓመት በፊት ነበር፡፡ አሜሪካ እያሉም ሥራቸውን እዛው በሚገኘው የአየር መንገዱ ቢሮወ ውስጥ ሲሰሩ እንደነበር መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
አቶ ተወልደ አየር መንገዱን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ለ11 ዓመታት መርተዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከኃላፊነት ባለፈም ተቋሙን በድምሩ ለ37 ዓመታትም አገልግለዋል፡፡
አቶ ተወልደ ሰራተኞቻቸው እስካሁን አብረዋቸው ስለሰሩ የምስጋና መልዕክት ጽፈውላቸዋል ተብሏል፡፡