የኢትዮጵያ አየር መንገድ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል ተብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ49 በመቶ ድርሻ የናይጄሪያ አየር መንገድን ለማቋቋም ተስማማ።
የአፍሪካ ትልቋ ባለ ብዙ ህዝብ ባለቤት የሆነችው ናይጀሪያ አሁን ላይ ብሔራዊ አየር መንገድ ከሌላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
ናይጄሪያ ከዚህ በፊት በፈረንጆቹ በ1958 የራሷን አየር መንገድ የገነባች ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ትርፋማ አለመሆኑን ተከትሎ ከ20 ዓመት በፊት ፈርሷል።
ይሄንንም ተከትሎ ናይጄሪያ ባለፉት ዓመታት የራሷን አየር መንገድ ለማቋቋም ብዙ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች።
አሁን ላይ ለበርካታ የአፍሪካ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች የራሷን የአቪዬሽን ተቋም እንዲያቋቁሙላት ጥሪ አቅርባ ነበር።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ49 በመቶ ድርሻ የናይጀሪያ አየር መንገድን ለማቋቋም የወጣውን ውድድር ማሸነፉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሀመዱ ቡሀሪ በ2015 ምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ ናይጄሪያ የራሷ አየር መንገድ እንዲኖራት አደርጋለሁ ብለው ቃል ገብተው ነበር።
በዚህም መሰረት ናይጄሪያ የራሷ ብሔራዊ አየር መንገድ ባለቤት ለመሆን በሂደት ላይ ስትሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ49 በመቶ ድርሻ ሲኖረው የናይጀሪያ ሉዓላዊ ፈንድ የተባለው ተቋም የ46 በመቶ እንዲሁም የናይጀሪያ መንግስት ደግሞ የአምስት በመቶ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።
በዚህ ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል ተብሏል።
አዲሱ አየር መንገድ የምዕራብ አፍሪካ ዋና የአሺዬሽን ማዕከል የመሆን እቅድ ያለው ሲሆን በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ 30 አውሮፕላኖች እንደሚኖሩት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ በፊት የማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ዛምቢያ እና ሎሎች የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶችን ድርሻ መግዛቱ ይታወሳል።
የአፍሪካ ግዙፍ የአቪዬሽን ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው 2014 ዓ.ም አምስት ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቻለሁ ማለቱ አይዘነጋም።