የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‘ጦር መሳሪያዎችንና ወታደሮችን ወደ ትግራይ አመላልሷል’መባሉን “መሰረተ ቢስ” ሲል አስተባበለ
በመግለጫው “በየትኛውም ወቅት ወደ ግጭት ቀጠናዎች የበረራ አገልግሎት ሰጥተን እንደማናውቅ ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲል አስታውቋል
አየር መንገዱ የማህበራዊ ሚዲያ አሉባልታዎቹን የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያ እና ወታደሮችን ወደ ትግራይ ክልል እያጓጓዘ እንደሆነ ተደርጎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች “እየተነገረ ያለው አሉባልታ መሰረተ ቢስ ነው” ሲል አስተባበለ፡፡
አየር መንገዱ “መሰረተ ቢስ ናቸው” ያላቸውን የማህበራዊ ሚዲያ አሉባልታዎች የተመለከተ መግለጫን አውጥቷል።
ወደ ትግራይ የሚደረጉ ሁሉም በረራዎች ከህዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ መቋረጣቸው የሚታወስ ነው ሲል ባስታወቀበት መግለጫው በመካከል የአየር ክልሉ ለአጭር ግዜ ተከፍቶ በነበረበት ወቅትም ከወታደራዊ አገልግሎት ውጭ የሆኑ አስፈላጊ የንግድ በረራዎች ብቻ ይካሄዱ ነበር ብሏል።
ወደ ክልሉ ይደረግ የነበረው በረራ ዳግም ከአንድ ወር በፊት መቋረጡ የሚታወቅ ነው ያለም ሲሆን “በየትኛውም ወቅት ወደ ግጭት ቀጠናዎች የበረራ አገልግሎት ሰጥተን እንደማናውቅ ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲል አስታውቋል።
አግባብነት ባላቸው የአቪየሽን አካላት እንደ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር አደገኛ ዕቃዎች ደንብ እና ሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ሕጎች እና ደንቦችን በጥብቅ የሚከተል እና የሚተገብር መሆኑን በማስታወስም በአለም አቀፍ የደህንነት ደረጃዎች እውቅና እንዳለውም ነው የገለጸው።
ሆኖም “እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ግለሰቦች አየር መንገዱ የገነባውን መልካም ስም ለማጉደፍ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ነባር እና የቆዩ ፎቶግራፎችን እና የተሳሳቱ ምስሎችን በፎቶሾፕ በማቀነባበር በመጠቀም ላይ ይገኛሉ” ነው ያለው አየር መንገዱ።
መለዮ ለባሾች (ወታደሮች) በህዝብ ትራንስፖርት መገልገላቸው የተለመደ ዓለም አቀፍ አሰራር ቢሆንም አየር መንገዱ ግን ጦርነት ወዳለባቸው አካባቢዎች አጓጉዟል ማለት አለመሆኑንም ለማሳወቅ እንደሚወድም ገልጿል።
የቀረቡበት ውንጀላዎች ሀሰተኛ፣ ከእውነት የራቁ እና መሰረተ ቢስ ስም የማጥፋት ዘመቻዎች መሆናቸውን ደንበኞቹ፣ የስራ አጋሮቹ፣ ባለድርሻ አካላት እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ እንዲያውቁለትም ጠይቋል፡፡