የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛሬ ጀምሮ የማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ማብረር ይጀምራል
ከ3 ዓመታት በፊት ባጋጠመው አደጋ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል
አየር መንገዱ ከባለፈው አስከፊ አደጋ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ማብረር የሚጀምረው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛሬ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ/ም ዕለተ ማክሰኞ ጀምሮ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ማብረር ይጀምራል፡፡
አየር መንገዱ ከባለፈው አስከፊ አደጋ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የቦይንግን የማክስ አውሮፕላኖች ማብረር የሚጀምረው፡፡
ከ3 ዓመታት ገደማ በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለመጓዝ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የተነሳው የበረራ ቁጥር 302 ማክስ 8 አውሮፕላን ከ6 ደቂቃዎች ጉዞ በኋላ ለእጅግ አስከፊ አደጋ መጋለጡ ይታወሳል፡፡
በፈረንጆቹ መጋቢት 10/2019 ረፋድ ላይ
ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ኤጀርሳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በደረሰው አስከፊ አደጋ የአውሮፕላኑን የበረራ ክፍል ባልደረቦች ጨምሮ የ157 ዜጎች ህይወት ማለፉም አይዘነጋም፡፡
አደጋው ከአውሮፕላኑ የምርት ሂደት ጋር የተያያዙ የቴክኒክ እክሎች ምክንያት ያጋጠመ እንደነበርም ቦይንግ ከወራት ማንገራገር በኋላ አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎ በርካታ አየር መንገዶች የማክስ 8 አውሮፕላኖችን ከበረራ ውጭ አድርገው ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማክስ አውሮፕላኖቹን ዳግም ወደ በረራ ለመመለስ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደቀሩት ከሰሞኑ አስታውቆ ነበር፡፡
የአሜሪካ የፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን /FAA/፣ የአውሮፓ ህብረት አቪየሽን ደህንነት ኤጀንሲ /EASA/፣ የቻይና እንዲሁም ሌሎች በርካታ የአቪየሽን ተቆጣጣሪ አካላት በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ ጥልቅ ምርመራና ፍተሻ ካደረጉና ዳግም ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ አውሮፕላኖቹን ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ ዳግም ወደ በረራ እንደሚመልስም አየር መንገዱ ለኤ.ኤፍ.ፒ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በአደጋው ወቅት 4 የማክስ 8 አውሮፕላኖች የነበሩት አየር መንገዱ 36 አየር መንገዶች የማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ማብረር መጀመራቸውን ጠቁሟል በመግለጫው፡፡
“ለደህንነት ቅድሚያ እንደመስጠታችንና ማክስ አውሮፕላንን ወደ ስራ ለመመለስ ከመጨረሻዎቹ አየር መንገዶች ተርታ እንደምንሆን በገባነው ቃል መሰረት እስካሁን 36 አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደበረራ በመመለስ ከ330 ሺህ በላይ በረራዎችን አድርገዋል” ሲል ነበር ቀደም ሲልም ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው፡፡
የአውሮፕላን አብራሪዎች፣ መሃንዲሶች፣ የአውሮፕላን ጥገና ባለሞያዎች እንዲሁም የበረራ አስተናጋጆች 737 ማክስ አውሮፕላኖቻችንን ወደ በረራ ለመመለስ ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅተዋልም ብሏል፡፡