የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋርጦ የነበረውን የባህር ዳር እና ጎንደር በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ
አየር መንገዱ አቋርጦት የነበረውን በረራ ከነገ ጀምሮ እንደሚጀምር ነው የገለጸው
በበርካታ የክልሉ ከተሞች ግጭት ተስተውሏል፤ በዚህም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋርጦት የነበረውን የባህር ዳር እና ጎንደር በረራ ከነገ ጀምሮ እንደሚጀምር አስታውቋል።
አየር መንገዱ ወደ ሁለቱ ከተሞች በራራ ያቋረጠው በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ነበር።
መደበኛ በረራው ነገ እንደሚጀምር የገለጸው አየር መንገዱ ተጓዦች በአቅራቢያዎች በሚገኙ ቢሮዎች ትኬት መቁረጥ እንደሚችሉም ገልጿል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር በአማራ ክልል መንግስት ልዩ ኃይልን ለማፍረስ የደረሰውን ውሳኔ ተከትሎ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በዚህ ሳምንት ተባብሷል።
በበርካታ የክልሉ ከተሞች ግጭቶች ተስተውለዋል፤ በዚህም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
የፌደራል መንግስት በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር አስችኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።
የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጠቅላይ መምሪያ እዙ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ የህግ ማስከበር ስራው በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ እና ክልሉ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት በውይይት እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንም በተመሳሳይ ችግሩ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ በውይይት እንዲፈታ አሳስቧል።