የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ በአማራ ክልል ስላለው ሁኔታ ምን አለ?
የእዙ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተመስገን “በተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ችግሮችን ፈጥሯል” ብለዋል
ህግ ማስከበር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናኑ መሆኑን አስታውቀዋል
በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለውን የህግ ማስከበር ተግባር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰለማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ አስታውቋል።
በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መጠየቁ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተገበር በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን፤ አዋጁን የሚያስተባብር ጠቅላይ መምሪያ እዝ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት ማብራሪያ፤ በክልሉ በተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አስተዳደራዊ ችግሮችን ፈጥሯል ማለታቸውን ኢዝአ ዘግቧል።
“ዘራፊ ቡድኖች የህዝብ አግልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ከማስተጓጎል ባሻገር በአንዳንድ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችን ሰብረው ወንጀለኞችን እንዲያመልጡ እስከማድረግ የደረሰ ውንብድና ፈጽመዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስ ለመቀልበስ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
“ቡድኑ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም ጭምር የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ መሆኑንም” ዋና ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ መንግስት ህግና ስርዓት የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጭምር ነው የተናገሩት።
በክልሉ እየተከናወነ ያለው የህግ ማስከበር ስራ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆም እና ሰራዊቱን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የሚኒስትሮች ምክርቤት በአማራ ክልል መደበኛ በሆነው የህግ ማስከበር መቆጣጠር አለመቻሉን እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጁ መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ጸንቶ ይቆያል።
በአማራ ክልል ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ መወሰኑን ተከትሎ የአማራ ልዩ ኃይል አይፈርስም የሚል ተቃውሞ በክልል ተካሂዶ ነበር። ይህን ተከትሎ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል።