ፕሬዝዳንቱ “በየትኛውም ወታደራዊ ዒላማዎቻችን ላይ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል
ዶ/ር ደብረጽዮን በአስመራ የተፈጸሙትን የሚሳዔል ጥቃቶች አረጋገጡ
የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) ሚሳዔል ትናንት ምሽት አስመራ ላይ “ተፈጽሟል” የተባለውን የሚሳዔል ጥቃት አረጋገጡ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለአሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የሚሳዔል ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠው “በየትኛውም ወታደራዊ ዒላማዎቻችን ላይ” እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን ምን ያህል ሚሳዔሎችን ወደ አስመራ እንዳስወነጨፉ ግን አልገለጹም፡፡
ሆኖም “አስመራ ብቸኛዋ የኤርትራ ዒላማችን ነች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱን በተመለከተ እስካሁን ከወደ ኤርትራ የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ የለም፡፡
ሆኖም የጥቃቱን በተመለከቱ የወጡ አንዳንድ ዘገባዎች “ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ስንል እንታገሳለን” የሚል አቋም በኤርትራ መንግስት በኩል እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
ህወሓት ከትናንት በስቲያ በባህርዳር እና ጎንደር ከተሞች ተመሳሳይ ጥቃቶችን መፈጸሙም ይታወሳል፡፡
ጥቃቱን አስመልክቶ በትግራይ ቴሌቪዥን ማብራሪያ የሰጡት የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና በክልሉ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ “በጎንደርም ሆነ በባህርዳር የተመረጡ ዒላማዎችን እናጠቃለን… በተጨማሪ በምጽዋም ሆነ በአስመራ የሚደረጉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማምከንም የሚሳዔል ጥቃቶችን የምናደርግ ነው የሚሆነው” ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡