በET-302 ማክስ 8 የመንገደኞች አውሮፕላን አደጋ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው
የ157 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበት የET-302 ማክስ 8 የመንገደኞች አውሮፕላን አደጋ ዛሬ ሁለተኛ ዓመት ሞልቶታል፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያዊያን ዘመን አቆጣጠር መጋቢት 10/2019 ረፋድ ላይ መነሻውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ መዳረሻውን ደግሞ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አድርጎ በረራ የጀመረው ET-302 መሬት በለቀቀ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ቢሾፍቱ ልዩ ስፍራው ቱሉ ፎራ በተባለ ቦታ ነበር የተከሰከሰው።
የቦይንግ ኩባንያ ምርት የሆነው አውሮፕላኑ የበረራ ክፍል አባላቱን ጨምሮ 157 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር።
በአደጋው ሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን የአደጋው መነሻ የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ባጠናው የምርመራ ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል።
ቦይንግ ኩባንያ መጀመሪያ ላይ ለአደጋው ሃላፊነት እንደማይወስድ የገለጸ ቢሆንም ዘግይቶ ግን ኩባንያው ጥፋቱን በማመን ለተፈጠረው አደጋ ሀላፊነት እንደሚወስድ ገልጿል።
በዚህ አደጋ መክንያት ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል ዘጠኙ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ 32ቱ ኬንያዊያን፣ 18ቱ ካናዳዊያን፣ 8ቱ ቻይናዊያን፣ 7ቱ ፈረንሳውያን፣ 6ቱ ከግብጽ፣ 5ቱ ከሆላንድ እንዲሁም 4ቱ ከህንድ እንደሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።
ቦይንግ ኩባንያ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ካሳ እንደሚከፍል ካሳወቀ በኋላ የክፍያ ሂደቱ አስካሁን አልተጠናቀቀም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአደጋው መከሰት በኋላ ማክስ 8 አውሮፕላኖችን እንዳይበሩ ያወረደ ሲሆን እገዳው አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።