ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትግስት አሰፋ በበርሊን የማራቶን ክብረ-ወሰን በመስበር አሸነፈች
በወንዶች ማራቶን ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ የራሱን ክብረ-ወሰን በመስበር አሸናፊ ሆኗል
አትሌቷ ያስመዘገበችው ሰአት ሶስተኛዋ የዓለማችን የርቀቱ ፈጣን ሯጭ ያደርጋታልም ተብሏል
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትግስት አሰፋ በበርሊን ማራቶን የቦታውን ክብረ-ወሰን በመስበር አሸነፈች፡፡
አትሌቷ ውድድሩን ያሸነፈችው 2:15:37 በሆነ ሰአት በመግባት ሲሆን የዓለም ሶስተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበች ሴት አትሌት መሆን መቻሏን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
በዘህም መሰረት አትሌት ትግስት አሰፋ እንደፈረንጆቹ 2019 በቺካጎ ማራቶን 2:14:14 የገባቸውን ኬንያዊት ብሪጊድ ኮስጋይን እና በ2003 በለንደን ማራቶን 2:15:25 በሆነ ሰዓት የርቀቱን አሻናፊ የነበረችውን እንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍን በመከተል ሶስተኛዋ የዓለማችን የርቀቱ ፈጣን ሯጭ ሆናለች፡፡
በርቀቱ ከአትሌት ትግስት አሰፋ ጋር ብርቱ ፉክክር ያደረጉት ኬንያዊቷ አትሌት ዋንጂሩ ሮስማሬ( 2:18:00) እና አትዮጵያውያን አትሌቶች ትግስት አባያቸው (2:18:03)፣ ወርቅነሽ እዴሳ (2:18:51) እና መሰረት ሲሳይ (2:20:58) ከ2ኛ አስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በሌላ ዜና ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በበርሊን ማራቶን የራሱን ክብረ-ወሰን በመስበር ጭምር ማሸነፉ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።
የ37 ዓመቱ አትሌት በዛሬው ዕለት በተካሄደው የበርሊን ማራቶን 2:01:09 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በአሸናፊነት ያጠነቀቀ ሲሆን ቀድሞ የነበረውን ሰዓት በ30 ሰኮንዶች በማሻሻል ክብረ-ወሰኑን መስበር ችሏል፡፡
በርቀቱ የተወዳደሩት የኢሉድ ኪፕቾጌ የሀገሩ ልጅ ኮሪስ ማርክ እና ኢትዮጵያዊው አትሌት አባተ ታዱም 2:05:58 እና 2:06:28 በሆነ ሰዓት 2ኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል፡፡
የ37 አመቱና የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ኪፕቾጌ በ17 የማራቶን ውድድር 15ኛ ድሉን ያስመዘገበ ሲሆን ይህም 26.2 ማይል (42 ኪ.ሜ) ርቀት ላይ በታሪክ ታላቁ ሯጭ ያደርጓል ተብሏል፡፡
ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንዳምላክ በልሁ እና ልመንህ ጌታቸው 4ኛ እና 6ኛ ደረጃ ይዘው ውድድራቸውን ጨርሰዋል፡፡
ዛሬ በጀርመኗ መዲና በርሊን በተካሄደው የማራቶን ውድድር ከ45ሺህ በላይ ሯጮች መሳተፋቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የበርሊን ማራቶን በየዓመቱ የሚካሄድና በዓለማችን ከሚታወቁ የማራቶን ውድድሮች ቀዳሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡