የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ
የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የደህነትና የፖሊስ ኃላፊዎችም በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል
ስምምነቱ የወታደራዊ ደህንነቶች መረጃ ልውውጥና ሌሎችንም እንደሚያካትት ተገልጿል
በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች መካከል የሁለትዮሽ የጋራ ስምምነት መፈረሙን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳስታወቀው የፊርማ ስነ ስርዓቱ የተደረገው 11ኛው የሁለቱ ሀገሮች የጋራ የኢታማዦር ሹሞች ስብሰባ በመኮንኖች ክበብ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው፡፡
ፊርማውን በኢትዮጵያ በኩል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላና በደቡብ ሱዳን በኩል የሀገሪቱ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ጆንሰን ጁማ ኡኮት ፈርመውታል፡፡
ስምምነቱም የወታደራዊ ደህንነቶች መረጃ ልውውጥን ፣ ድንበር ላይ የሚደረጉ ህገ ወጥ የሰዎች እና የጦር መሳሪያ ዝውውር መግታትን ፣ ወታደራዊ ዲፕሎማሲ ማጠናከርንና ሌሎችንም እንደሚያካትት ነው ተገለጸው፡፡ በደቡብ ሱዳን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ጆንሰን ጁማ ኡኮት የተመራው የደቡብ ሱዳን የመከላከያ ከፍተኛ ጀነራል መኮንኖች ልዑክ ፣ በትናንትናው ዕለት ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ተገናኝቶ በሀገራቱ ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ መምከሩ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የደህነትና የፖሊስ ኃላፊዎች በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡