ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያንና ሱዳንን በድንበሩ ጉዳይ ለማደራደር ዝግጅ መሆኗን ገለጸች
ፕሬዘዳንት ኪር ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የድንበር ውዝግብ በሰላም መፍታት እንዳለባት ገልጸው ነበር
ደቡብ ሱዳን የማደራደር ፍላጎቷን የገለጸችው የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የጸጥታ አማካሪ ከአልቡርሃን ጋር ተገናኝተዋል
ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸውን የድንበር ግጭት በሰላም እንዲፈቱ ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን ደቡብ ሱዳን አስታወቀች፡፡ደቡብ ሱዳን የድንበር ላይ ውዝግባቸውን በሰላም እንዲፈቱ መጠየቋ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ አዲስ አበባና ካርቱም የድንበር ላይ ውዝግባቸውን በሰላም ይፈቱ ዘንድ የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግ ገልጻለች፡፡
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት የጸጥታ አማካሪ ቱት ጋትሉዋክ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ጁባ ሀገራቱን ለማደራደር ዝግጁነቷን የገለጸችው፡፡
ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት አዲስ አበባና ካርቱም ችግሩን ፖለቲካዊና በዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ላይ በመመስረት እንዲፈቱና ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ በጸጥታ አማካሪያቸው በኩል አስታውቀዋል፡፡ ችግሩን በሚታወቀው ዓለም አቀፍ ድንበር መሰረት መፍታት እንዲቻል የማደራደር ሚና እንዲወጡ ነው የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት የገለጹት፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ችግሩ ወዳጅነትንና ወንድማማችነትን ተከትሎ እንዲፈታ ትኩረት ይደረጋል ማለታቸውን ሽንዋ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባሳለፍነው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ገልጸው ሱዳንም ይህንኑ ማስቀደም ብትችል ለሁለቱ ሀገራት የቆየ ወዳጅነት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት አባል የሆኑትን ቼምስ አል ዲን ካባሽ እና ተጠባባቂ የሱዳን ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ቀመረዲንን በጁባ ባነጋገሩበት ወቅት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የድንበር ውዝግብ በሰላም መፍታት እንዳለባት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዚዳንት ኪር ካርቱምና አዲስ አበባ የድንበር እሰጥ አገባውን በድርድርና በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፍታት እንዳለባቸው መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ሀገራቸው ሁለቱን ጎረቤታሞች ለማደራደር ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡