“የሱዳንና የግብፅ አካሄድ ከአሁን በፊት የመጣንበትን ሂደት ፉርሽ የሚያደርግ ነው” ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
የግድቡ ግንባታ በሚቀጥለው ክረምት 2ኛ ዙር ውሃ ለመያዝ በታቀደው መሰረት እየተከናወነ እንደሚገኝም አንስተዋል
ሱዳን እና ግብፅ ስም በማጥፋት ተጽዕኖ ለማድረግ እንደሚሞክሩ ሚኒስትሩ ገልጸዋል
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በዕቅድ መሰረት እየተከናወነ እንደሚገኝ የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ የሕዳሴ ግድቡን የግንባታ ሂደት እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሦስትዮሽ ድርድሩን በተመለከተ “የሱዳንና የግብፅ አካሄድ ከአሁን በፊት የመጣንበትን ፉርሽ የሚያደርግ ነው” ብለዋል፡፡ “ሁለቱም ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች አላቸው” ያሉት ሚኒስትሩ “እኛ ታማኝ ሆነን እየተደራደርን ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ባለፉት 7 የሕብረቱ ድርድሮች ኢትዮጵያ የምትጠየቅበት የተለየ ነገር እንደሌለም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት፡፡ እንደ ዶ/ር ስለሺ ገለጻ ፣ በኢትዮጵያ በኩል “መጀመሪያ ስለሙሌቱ ተስማምተን እንቀጥል” የሚል ሀሳብ ቢቀርብም ፣ ግብፅ እና ሱዳን “ሙሉ ስምምነት ነው የምንፈልገው” በሚል አልተቀበሉትም፡፡
በድርድሩ ወጥ አቋም እንደሌላቸው የሚታሙት ሁለቱ ሀገራት “ስም በማጥፋት ተጽዕኖ ለማድረግ” እንደሚሞክሩም የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ የተናገሩ ሲሆን ይህ ድርጊታቸው “ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚታገለው ነው” ብለዋል፡፡
የሚኒስትሩ ገለጻ እንደሚያሳየው የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም 78 ነጥብ 3 በመቶ የደረሰ ሲሆን የሲቪል ስራዎች አፈጻጸም ደግሞ 91 በመቶ ደርሷል።
የግድቡ ግንባታ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ከነበረበት አፈጻጸም የ4.05 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ሚኒስትሩ የተናገሩ ሲሆን ክረምቱ እስኪገባ በቀጣይ ወራት የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማሳካት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።