“ዋሽንግተን በመሄዳችን የተዛቡ ነገሮችን እንዲስተካከሉ አድርገናል”- ሚኒስትር ስለሺ (ዶ/ር)
ሶስቱ ሀገራት ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በቴክኒክ ኮሚቴያቸው በኩል ለመጀመር ባለፈው ሳምንት ስምምነት ላይ ደርሰዋል
ሚኒስትሩ ስለሺ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለድርድር አሜሪካ መሄዷ አለው ያሉትን ጥቅም ለፖለቲካ ፓርቲዎች አስረድተዋል
ሚኒስትሩ ስለሺ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለድርድር አሜሪካ መሄዷ አለው ያሉትን ጥቅም ለፖለቲካ ፓርቲዎች አስረድተዋል
ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጽና ሱዳን ጋር በአሜሪካ ዋሽንግተን ያደረገችው ድርድር ”…የተዛቡ ነገሮች እንዲስተካከሉ” የረዳት ሲሆን ጥቅሟ ሲነካ ደግሞ ጥላ መውጣቷን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ( ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በግድቡ የግንባታ ሂደት ዙሪያ ዛሬ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
በፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና በግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ የገለጻ ፕሮግራም ላይ የህዳሴው ግድብ የግንባታ ደረጃና የግድቡ የድርድር ሂደትን በተመለከተ ማብራያዎች ተሰጥተዋል፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በሦስቱ ሀገራ ያደረጓቸውን የድርድር ሂደቶች ለፖለቲከኞቹ አስረድተዋል፡፡ኢትዮጵያ በየትኛውም ቦታና ሁኔታ የመልማትና ህዝቧን የመለወጥ ፍላጎት እንጅ ማንንም ለመጎዳት ብላ ግድብ እንደማትገነባ በየውይይቶቹና ድርድሮቹ ላይ መገለጹን አንስተዋል፡፡ “አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በታዛቢነት መሳተፋቸው ትክክል አልነበረም፣ወደ ዋሸንግተን መሄዳችንም ትክክል አይደለም” የሚሉ ሃሳቦች እንደነበሩ ያነሱት ኢ/ር ስለሺ በቀለ “ወደ አሜሪካ በመሄዳችንም ብዙ ጥቅም አግኝተናል” ብለዋል፡፡
መሰረታዊ የሚባሉ ዕውነታዎችን ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት መግለጻቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ የሕዳሴ ግድቡ ከዓለም አንደኛ ነው የሚሉ የተዛቡ መረጃዎችን “ግብጽ ለአሜሪካኖች መናገሯንና” ይህም ትክክል እንዳልሆነ ለማስረዳት ዕድሉን መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡ ኢ/ር ስለሺ በዋሸንግተኑ መድረክ የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር በሚገባ ለማስረዳት መቻሉንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያም በራሷ ሀብት የመጠቀም መብቷን ተጠቅማ በወንዟ ላይ ግድብ እየገነባች መሆኑን ለመግለጽ ዕድል መገኘቱን ያሱት ኢ/ር ስለሺ በቀለ “አሜሪካ ከታዛቢነት ሚናዋ ስታፈነግጥና ጫና ማሳደር ስትፈልግና ስትሞክር ግን ውይይቱን ረግጠን ወጥተናል “ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከመጀመሯ አስቀድሞ የዲፕሎማሲ ስራዎችን መስራቷን ገልጸው ይህም አሁን ላይ ተጠናክሮ እንደቀጠለ አንስተዋል፡፡
“የተፈጥሮ ሃብታችንን ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የማንንም ፍቃድ መጠየቅ አያስፈልገንም፣ የግድቡ ግንባታ ሌሎች ላይ የጎላ ተጽዕኖ የማድረስ ዓላማ የለውም፤ የመጉዳት ዓላማ እንደሌለው ለዓለምአቀፋ ማኅበረሰብ የማሳወቅ ስራ ተሰርቷል“ብለዋል፡፡
የፖለቲከ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሙሳ አደም ማናቸውም የፖለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩም ሁሉም ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች በሕዳሴው ግድብ ላይ አንድነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ጥሪ ከተደረገላቸው መካከል ጉዳዩን ያዘጋጀው መንግስት ነው በማለት ያልተገኙ መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችም አንገኝም ብለው የቀሩ ፓርቲዎች ስም ይነገር የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰብሳቢው አቶ ሙሳ ይህንን ድርጊት ከደገሙትና በብሔራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት ፈቃደኛ የማይሆኑት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡
ፖለቲከኞቹ አሁን ላይ ሁሉም ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፖርቲዎች ከምንም በላይ በግድቡ ላይ ያለውን አንድነት በተግባር የሚያሳዩበት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከሀገር ሉዓላዊነት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ ባለመኖሩ ሁሉም ዜጋ ከውጭ የሚመጣውን ተጽዕኖ በጋራ መመከት እንደሚገባው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታው ሂደት 73.7 በመቶው መጠናቀቁን ውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒትሩ ስለሺ በቀለ ገልጸዋል፡፡
የግድቡን መገንባት ስትደግፍ የነበረችው ሱዳን ኢትዮጵያ በመጭው ሀምሌ ወር ያቀደችውን የግድቡን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት አልደግፍም የሚል አቋም አንጸባርቃለች፡፡ ግብጽ በአንጻሩ ከግድቡ የመሰረት ድንጋይ መጣል ጀምሮ የሚደርሰኝ የውሃ መጠን ይቀንሳል በማለት ተቃውሞዋን እያሰማች ቆይታለች፤ የግድቡን የውሃ ሙሌቱ እቅድንም አትቀበለውም፡፡
ሶስቱ ሀገራት ወቅታዊ በሆነው አቋማቸው፤ የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች የተቋረጠውን ድርድር ለመጀመር ተስማምተዋል፡፡