የቱሪዝም ሚኒስቴር ቅርሶቹን ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱ ተገልጿል
የእንግሊዝ ጦር ከ153 ዓመታት በፊት ከመቅደላ ዘርፎ ከወሰዳቸው የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል በብሪትሽ ሙዝየም የነበሩ 13 የተለያዩ ቅርሶች መመለሳቸው ተገለጸ፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ ቅርሶቹን ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለስ ቅርሶቹን ይዘው መጥተዋል፡፡ ቅርሶቹን የቱሪዝም ሚንስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ እና የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና የዳይሬክተር አበባው አያሌው ተቀብለዋል፡፡
ከእንግሊዝ የተመለሱት ቅርሶች በብሔራዊ ሙዝየም እንዲቀመጡ መደረጉም ተገልጿል፡፡
የእጅ መስቀል፣ ዘውድ፣ የጸሎት መጽሃፍት፣ መጠጫዎች እና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ቅርሶች ከተመለሱት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ቅርሶቹን ለማስመለስ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ በእንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ቅርሶቹ በአግባቡ ተጠብቀው ለጎብኝዎች ክፍት እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር ለጥናትና ምርምር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡
በጦርነቱ ወቅት የተወሰዱና በእንግሊዝ ሙዚየም የተቀመጡ ቅርሶች የአጼ ቴዎድሮስን ጸጉር ጨምሮ በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡