ታሪካዊ ቅርሶችንና ተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ገለፀ
ህወሓት በአማራ ክልል አካባቢዎች የከፈተው ጥቃት እድሜ ጠገብ ቅርሶች ላይ የደህንነት ስጋት ደቅኗል ብሏል
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የህወሃት ቡድንን የጥፋት ድርጊት እንዲያወግዝም መንግስት ጥሪ አቅርቧል
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችንና ተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ገለፀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አሸባሪ በሚል የፈረጀው የህወሃት ቡድን መንግሥት እርዳታ ተደራሸ እንዲሆንና አርሶ አደሩ የዝናብ ወቅቱን በመጠቀም የግብርና ስራውን እንዲያከናዉን በማሰብ የወሰደዉ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን ወደ ጎን መተውን ጠቅሷል።
እንዲሁም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ የቀረበለትን የተኩስ አቁም ጥሪ ቸል በማለት ትንኮሳውን መቀጠሉንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የሽብር ቡድኑ በአዋሳኝ ክልሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የእርዳታ አቅርቦትን በማስተጓጎል ሚሊዮኖችን አደጋ ላይ መጣሉንም ነው ያስታወቀው።
በቅርቡ በተወሰኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች በከፈተው ጥቃት ቡድኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የባህል፣ የእምነት እና የማንነት መገለጫ በሆኑ እድሜ ጠገብ ቅርሶች ላይ የደህንነት ስጋት ደቅኗልም ብሏል ሚኒስቴሩ።
ስጋቱ ቡድኑ ባለፉት ስምንት ወራት ከፈጸመው መሰል ዝርፊያና ውድመት ተግባሩ የሚመነጭ መሆኑንም ጠቅሷል።
በአገሪቱ የሚገኙ ቅዱሳ ቦታዎች እና ተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ በሚል የፈረጀው የህወሓት ቡድንን የጥፋት ድርጊት እንዲያወግዝም መንግስት ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ በሚል የፈረጀው ህወሓት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘውን የላሊበላ ከተማ አስተዳደርን ባሳለፍነው ሀሙስ መቆጣጠሩን መናገሩ ይታወሳል።
የህወሓት ሀይሎች ላሊበላ ከተማን ባሳለፍነው ሀሙስ እኩለ ቀን አካባቢ ከተቆጣጠሩ በኋላ በከተማዋ በሚገኙ 3 ትምህርት ቤቶች ካምፖችን ሰርተው መቀመጣቸውን የከተማዋ ነዋሪ በዕለቱ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጣው መግለጫ፤ ላሊበላ ከተማ የገባው የህወሓት ቡድን አሁን ላይ በመከላከያ ሰራዊትና በክልሉ ልዩ ሃይል እየተመከተ መሆኑን አስታውቋል።
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መንግስት ሀገ ረመንግስቱን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ላይ ተሳትፏል ያለውን ህወሓትን በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል፡፡
በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስትና ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ግጭት ከተጀመረ ከ8 ወር በኋላ የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት ሰራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው አርሶ አደሮች ወደ ገበርና ስራቸው እንዲመለሱ እና ለህዝቡ የጥሞና ጊዜ በመስጠት ቀውሱን በውይይት ለመፍታት በማቀዱ መሆኑን ቢገልጽም ግጭቱ አሁን ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፏፍቷል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋውን ጥቃት መከላከያ ሰራዊትና የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ አካላት የህወሓትን እንቅስቃሴ ለመግታት ጥቃት መክፈታቸውም መንግስት አስታውቋል፡፡