ሩሲያ የፕሬዝዳንት ፑቲን "የክተት አዋጅ”ን የተቃወሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን እያሰረች ነው
የክሬምሊን ባለስልጣናት እስከሁን ከ700 በላይ ተቃውሞ ያሰሙ ሰዎች ማሰራቸው ተገልጿል
በፖሊሶች የተወሰደች አንዲት ሩሲያዊት ሰልፈኛ "እኛ የመድፍ መኖ አይደለንም" ስትል ተሰምታለች
የክሬምሊን ባለስልጣናት ሰሞኑን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያቀረቡትን ከፊል የክተት ጥሪን የተቃወሙ ለ700 በላይ ሩሲያውያን ማሰራቸው ገለልተኛ የመብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ።
እስካሁን በ32 ከተሞች ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረጋቸው ቢያንስ 726 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ግማሾቹ በሞስኮ ውስጥ ይገኛሉ ተብለዋል።
አሁን ላይ በሞስኮ ቺስቲ ፕሩዲ መሃል አካባቢዎች ከፍተኛ የፖሊስ አባላት ስምሪት እንዳለም የኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል፡፡
አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች በፖሊስ እንዳይታዩ እና እንዳይታሰሩ - በተናጥል ወይም በቡድን - በእግራቸው ሲሄዲና ሲቃወሙ ነበር ያለው ዘገባው ፖሊሶች ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎችን አስረዋልም ብሏል፡፡
አንዲት ሰልፈኛ ፖሊሶች ሲወስዷት "እኛ የመድፍ መኖ አይደለንም!" ስትል ተቃውሞዋን በጭሆት ስትገለጽ እንደነበርም ዘገባው አመላክቷል፡፡
በሩሲያ ሁለተኛዋ የሴንት ፒተርስበርግ ከተማ 30 የሚጠጉ እስረኞችን የያዘ የፖሊስ ቫን ማየቱም በሩሲያ የሚገኘው የኤኤፍፒ የዜና ወኪል ምስክርነቱ ሰጥቷል፡፡
ሌላው “ሰላም” የሚል ምልክት ይዞ የነበረው የ22 ዓመቱ ኢሊያ ፍሮሎቭ በበኩሉ ለፑቲን ተብሎ የሚከፈል መስዋዕትነት የለም ሲል ተሰምቷል፡፡
"እየሆነ ላለው ተቃውሞዬን ማሰማት እፈልጋለሁ...ለፑቲን ብየ ጦርነት ውስጥ መግባት አልፈልግም" ሲልም ተናግሯል።
"ጦርነትን እና ቅስቀሳን እቃወማለሁ…. ለወጣቶች (ዝመቱ እንዳይባሉ) እፈራለሁ" ሲሉ የተደመጡት ደግሞ የ 70 ዓመቷ ናታሊያ ዱቦቫ ናቸው፡፡
የሩሲያ ድርጊት ከሀገሬው ዜጎች ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድረስ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ቢሆንም፤ የክሬምሊን ባለስልጣናት ግን ድርጊቱ "ህጋዊና አግባብነት ያለው ነው" እያሉ ነው፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የክተት አዋጁን ተከትሎ ሩሲያውያን ወጣቶች ከሀገሪቱ ለመውጣት መሸሽ ቀጥለዋል።
ሀገሪቱን ከጆርጂያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር የሩሲያ መኪኖች ወረፋ ከ 30 ኪ.ሜ በላይ ሆኗልም ነው የተባለው።
በአካባቢው ያሉ የሩሲያ ባለስልጣናት ለመሻገር የሚሞክሩ ከፍተኛ መኪኖች መጉረፋቸውን አምነዋል።
ወደ 2 ሺህ 500 የሚጠጉ መኪኖች በአንድ የፍተሻ ጣቢያ ብቻ ወረፋ እየጠበቁ ነው።
የክሬምሊን ባለስልጣናት ፤ ሩሲያውያንን ወጣቶች እየሸሹ ነው የሚለውን ዘገባ “ሐሰት” ነው ብለውታል፡፡
በተቃራኒው የክተት ጥሪውን የሚቃወሙት እንዳሉ ሁሉ፤ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያቀረቡትን የክተት ጥሪ ተከትሎ በርካታ ሩሲያውያን ፈቃደኝነታቸው እንዳሳዩም ይታወቃል፡፡
የክተት ጥሪውን ተከትሎ በአንድ ቀን ብቻ 10 ሺህ ሩሲያውያን ለመዝመት ፈቃደኛ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡