አዲሱ መንግስት የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር ካልቻለ ሀገር ችግር ውስጥ ትገባለች- አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ
በቶኪዮ ኦሎምፒክ ውጤት የተጎዳውን ህዝብ በቀጣይ ሊክስ የሚችል ዝግጅት እንዲጀመርም አትሌቱ አሳስቧል
ብልጽግና ፓርቲ በሰኔው ምርጫ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ በትናንትናው ዕለት አዲስ መንግስት መስርቷል
አዲሱ መንግስት የስራ እድል ፈጠራ ላይ ካልሰራና እና የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር ካልቻለ ሀገር ችግር ውስጥ እንደምትገባ ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ተናገረ።
ያሳለፍነው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ወንበር ማግኘቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በትናንትናው ዕለት በይፋ ተመስርቷል።
የህዝብ ተወካዮች መክር ቤት በመጀመሪያ ጉባኤው አብይ አህመድን (ዶክተር) ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መርጧል፡፡ በምክር ቤት ጉባኤ ላይ በተጋባዥነት አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ሌሎች አካላትም ተገኝተው ነበር።
አል ዐይን አማርኛ ከአትሌት ሀይሌገብረስላሴ ጋር ባደረገው ቆይታም የስራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነት ለአዲሱ መንግስት ዋነኛ ስራዎች ሊሆኑ ይገባል ሲል ተናግሯል።
“ላንድ አገር ትልቁ ራስምታት ኑሮ ውድነት እና ስራ አጥነት ናቸው። እነዚህ ደግሞ የእኛ ዋነኛ ችግሮቻችን ናቸው። እነዚህን ችግሮች እንደ ሀገር መፍታት ካልቻልን ችግር ውስጥ መግባታችን አይቀሬ ነው። አዲስ መንግስት መመስረት ዋነኛ ግብ አይደለም። ዜጎቻችንን ከድህነት ማውጣት አለብን ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ከመንግስት ብቻ አይጠበቅም ሁላችንም የሚጠበቅብንን ማድረግ አለብን” ሲልም አክሏል አትሌት ሀይሌገብረስላሴ።
አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ሌላኛው አስተያየቱን ያጋራን ጉዳይ ከስፖርት አንጻር ነው።
“ባሳለፍነው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ህዝባችንን የማይመጥን ውጤት ነው የተገኘው፤ በመሆኑም አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ካሁኑ ለቀጣዩ ኦሎምፒክ በቂ ዝግጅት በማድረግ ህዝባችንን የሚመጥን እና የሚክስ ውጤት ማምጣት የሚያስችል አሰራር መከተል ያስፈልጋል” ብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በዓለ ሲመት በትናንትናው እለት በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል፡፡
በበዓለ ሲመት መርሃግብሩ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡የኬንያው ኡሁሩ ኬንያና፣የናይጀሪያው ሞሀመድ ቡሃሪ፤ የኡጋዳው ዮሪ ሞሰቨኒና የሰቡብ ሱዳኑ ሳለቫኪል ከተገኙት መሪዎች መካከል ናቸው፡፡