በጋና እየተካሄደ ባለው አህጉር አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 5 የወርቅ ሜዳሊያ አገኙ
እስካሁን በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ ስምንት ሜዳሊያ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
በጋና ዋና ከተማ አክራ እየተካሄደ ባለው 13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አምስት የወርቅ ማግኘታቸውን ፌደሬሽኑ ገለጸ
በጋና ዋና ከተማ አክራ እየተካሄደ ባለው 13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አምስት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በፌስቡክ ገጹ እንዳስታወቀው እስካሁን በተካሄዱ ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፉት አትሌቶች ሳሙኤል ፍሬው፣ መዲና ኢሳ፣ፅጌ ዱጉማ፣ ንብረት መላክ፣ እና ምስጋና ዋቁማ ናቸው።
አትሌት ሳሙኤል ፍሬው በ3000 ሜትር መሰናክል ሩጫ 8:24:30 ደቂቃ በመግባት የመጀመሪያውን ወርቅ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል።
አትሌት መዲና ኢሳ በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜን በ15:04.32፣ ፅጌ ዱጉማ በ800 ሜትር ሴቶች ፍጻሜን በ1:57.73 ፣ ንብረት መላክ በ10000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜን በ29:45.37 ደቂቃ በመጨረስ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፋቸውን ፌደሬሽኑ ገልጿል።
ዛሬ ረፋድ በተካሄደው የ20 ኪሎሜትር የእርምጃ ውድድር የተሰለፈው ምስጋና ዋቁማም የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱን ፌደሬሽኑ ጠቅሷል።
ብርቱካን ሞላ በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ፣ ገመቹ ዲዳ በ10000 ሜትር የወንዶች ፍጻሜ እና ሰንታየሁ ማስሬ በሴቶች የ20 ኪሎሜትር እርምጃ ውድድር የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።
እስካሁን በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ ስምንት ሜዳሊያ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።