ጀርመን ባወጣችው አዲሱ ህግ መሰረት ሰዎች ለግል ፍጆታ እስከ 20 እስከ 30 ግራም የመዝናኛ ካናቢስ መያዝ ይችላሉ
ጀርመን በመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ መንግስት በተገባው ቃል መሰረት ካናቢስን ለመዝናኛ ዓላማ ህጋዊ ለማድረግ እቅድ ማውጣቷ ተገለጸ።
የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ካርል ላውተርባች የካናቢስ ስርጭት እና በአዋቂዎች መካከል ለመዝናኛ አገልግሎት የሚውሉበትን ሁኔታ ለመቆጣጠር ያስችላል ያሉትን ረቂቅ ህግ አቅርበዋል።
ጀርመን ባወጣችው አዲሱ ህግ መሰረት ሰዎች ለግል ፍጆታ እስከ 20 እስከ 30 ግራም የመዝናኛ ካናቢስ ማግኘት እና መያዝ ይችላሉ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የጥምረቱ መንግስት ፍቃድ በተሰጣቸው ሱቆች ውስጥ በመጠኑ የሚታወቅ የካናቢስ ስርጭቶ እንዲኖር በአራት-ዓመት ጊዜ ውስጥ ህግን ተግባራዊ ለማድረግ ባለፈው አመት ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም።
እቅዱ መች ተግባራዊ እንደሚደረግ ግልጽ ያላደረጉት የጤና ሚኒስትሩ ላውተርባክ እርምጃው ጀርመን ከማልታ ቀጥሎ ካናቢስን ሕጋዊ በማድረግ ሁለተኛዋ የአውሮፓ ህብረት ሀገር የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ጀርመንን ጨምሮ ብዙ የአውሮፓ ሀገራት ካናቢስን ለተወሰኑ የህክምና ዓላማዎች ሕጋዊ አድርገዋል።
ሌሎች ደግሞ አጠቃላይ አጠቃቀሙን ህጋዊ እስካላደረጉ ድረስ ወንጀል አድርገውታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ ምስራቅ እስያዋ ታይላንድ ዜጎቿ በህጋዊ መንገድ ካናቢስ እንዲያመርቱና እንዲሸጡ የሚያስችል የህግ ማሻሻያ ከወራት በፊት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
ታይላንድ ይህንን ማሻሻያ ስታደረግ ጠንካራ የሚባል የእጽ ህግ ባለበት ደቡብ ምስራቅ እስያ አከባቢ ከሚገኙ ሀገራት ቀዳሚዋ ናት።
ይሁን እንጅ ታይላንድ ከጀርመን በተለየ መልኩ እጽ እንደ መዝናኛ መጠቀምና በየአደባባዩ ማጨስ ትከለክላለች።