ኢትዮጵያ በግድቡ ጉዳይ ስምምነት እንዳይደረስ ግብጽ እንቅፋት ሆናለች ስትል ወቀሰች
ግብጽ ኢትዮጵያ ምንም አይነት የህግ እና የቴክኒክ ጉዳዮች ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆኗ ድርድሩ አለመሳካቱን ገልጻለች
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ግብጽ "የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብን" በመያዟ ድርድሩ ወደ ስምምነት እንዳይመጣ እንቅፋት ፈጥራለች ብሏል
ግብጽ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው አራተኛው ዙር ድርድር መጠናቀቅ ተከትሎ ባወጣችው መግለጫ ኢትዮጵያ ምንም አይነት የህግ እና የቴክኒክ ጉዳዮችን ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆኗ ድርድሩ አለመሳካቱን ገልጻለች።
ኢትዮጵያ በአንጻሩ ድርድሩ ያልተሳካው በግብጽ ምክንያት ነው የሚል መልስ ሰጥታለች።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ግብጽ "የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብን" በመያዟ ድርድሩ ወደ ስምምነት እንዳይመጣ እንቅፋት ፈጥራለች ብሏል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን አራተኛውን የሶስትዮሽ ድርድር ሰኞ እና ማክሰኞ በአዲስ አበባ አካሂደዋል።
ይህ አራተኛው ዙር ድርድር የተካሄደው ባለፈው ሀምሌ ወር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የግብጹ ፕሬዝደንት አል ሲሲ በካይሮ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ነበር።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው መሪዎቹ በግድቡ ሙሌት ዙሪያ የሁለቱም ሀገራት ባለሙያዎች እንዲመክሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ነው በአዲስ አበባ ለድርድር የተቀመጡት።
ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረት አድርጋለች ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብጽ በምታራምደው አቋም ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል።
ሚኒስቴሩ በሙሌት እና በአመታዊ አስተዳደር ህጎች እና መመሪያዎች ላይ የሚደረገው ድርድር በሶስቱ ሀገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር እንጅ የኢትዮጵያን ውሃ የመጠቀም መብት ለመገደብ እንዳልነበር ገልጿል።
ሶስቱ ሀገራት በፈረንጆቹ 2015 'የመርሆች ስምምነት' ከተፈራረሙ ወዲህ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ እስካሁን ስምምነት ላይ አልደረሱም።
የግድቡን የድርድር ሂደት ለራሷ በሚጠቅም መልኩ እየተጠቀመችበት ነው ስትል በኢትዮጵያ ላይ ክስ ያሰማችው ግብጽ፣ የግድቡን እና ሪዘርቪየሩን ሙሌት እና አስተዳደር በአለምአቀፍ ህግ መሰረት የውሃ መብቷን ለማስጠበቅ ስትል እንደምትከታተለው ገልጻለች።
ኢትዮጵያ በበኩሏ የግብጽ አካሄድ የተመድን ቻርተር የሚጥስ ነው የሚል ምላሽ ሰጥታለች።
የኢትዮጵያ የግድቡ ዋና ተደራዳሪ ዶክተር ስለሺ በቀለ በሰጡት መግለጫም የድርቅ ወቅት የውሃ አያያዝ ጉዳይ ከስምምነት ሊደረስበት እንዳልቻለ አብራርተዋል።
ግብጽና ሱዳን የቀደመና ኢትዮጵያን ያገለለ የውሃ ኮታ ስምምነታቸውን ይዘው በመምጣት ኢትዮጵያ እንድታጸድቅላቸው የሚያቀርቡት ጥያቄ በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው በመጥቀስም ለ4ኛው ዙር ድርድር በስኬት አለመጠናቀቅ ካይሮን ወቅሰዋል።