ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በፊት የግድቡን 4ኛ ዙር ውሃ ሙሌት ማጠናቀቋ አይዘነጋም
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በአዲስ አበባ ተጀመረ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሦስትዮሽ ሁለተኛ ዙር ውይይት ተጀምሯል፡፡
ሁለተኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦች እና መመሪያዎች የሶስትዮሽ ድርድር በአዲስ አበባ እየተካሄደ መሆኑን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ወገን ተደራዳሪዎች ልኡካን መሪ አምባሳደር ስለሽ በቀለ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ይህ ውይይት እየተካሄደ ያለው እ.ኤ.አ. በ2015 በተደረሰው የመርሆዎች መግለጫ መሰረት ከተከናወነው አራተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በኋላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም፣ በዚህ ዙር ውይይት አገራቱ በጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ ለመድረስ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አያይዘውም በመርሆዎች መግለጫው በተቀመጠው መሰረት በአባይ ውሃ አጠቃቀም ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ማስፈን ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም አምባሳደር ስለሺ ገልጸዋል ተብሏል።
የግብጽ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ፕ/ር ሐኒ ሴዊላም እና የሱዳን ተጠባባቂ የውሃ ሚኒስትር ዳውልበይት አብድልረህማን ማንሱር ባሽር በመክፈቻ ንግግሮቻቸው በድርድሩ ሒደት ስምምነት ለመድረስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በፊት የግድቡ አራተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ሚኒስተር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ ለመቀንስ ወሰነች
ግብጽ በበኩሏ የኢትዮጵያ ውሃ ሙሌት የተናጥል ድርጊት መሆኑን ጠቅሳ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ተቃውማለች፡፡
ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ በሱዳን ለተከሰተው ጦርነት እልባት ለመፈለግ በሚል በካይሮ በተካሄደው የጎረቤት ሀገራት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ሲመክሩም ይሄው የህዳሴው ግድብ ጉዳይ አንዱ አጀንዳ ነበር።
በዚህ ምክክር መሪዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየውን የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዳግም ለመጀመር መስማማታቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።