ከሁለተኛው የህዳሴው ግድብ ድርድር በኋላ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ምን አሉ?
ሶስተኛው የሶስትዮሽ የቴክኒክ ባለሙያዎች ድርድር ከአንድ ወር በኋላ በካይሮ ይካሄዳል ተብሏል
ግብጽ የሶስቱንም ሀገራት የመልማት ፍላጎት እንደምታከብር ገልጻለች
ከሁለተኛው የህዳሴው ግድብ ድርድር በኋላ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ምን አሉ?
ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ በሱዳን ለተከሰተው ጦርነት እልባት ለመፈለግ በሚል በካይሮ በተካሄደው የጎረቤት ሀገራት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን ለማስቀጠል መስማማታቸው ተገልጾ ነበር፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት ከሶስት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የግድቡ ተደራዳሪ የቴክኒክ ባለሙያዎች በግብጽ ካይሮ ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል፡፡
ሁለተኛው ዙር የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት ደግሞ ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ትናንት እሁድ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የግድቡ ተደራዳሪዎች፣ ባለሙያዎች እና ዲፕሎማቶች የተሳተፉበት ይህ ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱም ሀገራት በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የግብጽ ውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ሀኒ ስዌለም እንዳሉት በአዲስ አበባ የተካሄደው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም የህዳሴው ግድብ ድርድርን በአወንታዊ እና መልካም ጎኑ እንደወሰዱት ተናግረዋል፡፡
የግብጽ ፍላጎት ሚዛናዊ እና ፍትሃዊ የውሃ ፍላጎት ማስፈን የሚያስችል ስምምነት እንዲኖር ነው ያሉት ሚኒስትሩ የሶስቱ ሀገራት የጋራ ልማትን እንደሚደግፉም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ኢጅፕት ኢንዲፐንደንት ዘገባ ከሆነ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የተናጠል ውሳኔዎችን በመወሰን የግድቡን ውሃ መሙላቷን የተቃወሙ ሲሆን የተናጠል ውሳኔዎች የሶስትዮሽ ድርድሩን ይጎደዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በአዲስ አበባ የተካሄደው ሁለተኛው የሶስትዮሽ ድርድር በስኬት መጠናቀቁት እና ሶስተኛው ድርድር የፊታችን ጥቅምት ወር ላይ በግብጽ ካይሮ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡
ይሁንና ግብጽ አሁንም በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ስምምነቶች እንዲከበሩ መጠየቋ እንዳሳዘነው የገለጸው የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2015 በተደረሰው የመርሆች ስምምነት መሰረት በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መንገድ ወደ ስምምነት መምጣት እንዲቻል ጥረቷን እንደምትቀጥል አስታውቋል፡፡
መግለጫው አክሎም ኢትዮጵያ የአሁኑን እና የቀጣዩን ትውልድ የውሃ ፍላጎት መሰረት ያደረገ የሶስትዮሽ ውይይት ለማድረግ ጥረት ማድረጓን ጥቀጥላለችም ብሏል፡፡
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአዲስ አበባ የተካሄደው ሁለተኛው የሶትዮሽ ውይይት በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ስለሺ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገጻቸው እንዳሉት “በሀገራቱ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ ድርድርና የሃሳብ ልውውጥ ተካሂዷል:: ኢትዮጵያ የጋራ መፍትሄ ላይ ለመድረስ በቀና መንፈስ አበክራ ትሰራለች” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አራተኛው ዙር የህዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡
በሀይል የማመንጨት አቅሙ ከአፍሪካ አንደኛ የሆነው ይህ ግድብ እስካሁን ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።