በካይሮው የተካሄደው የባለሙያዎች ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁ አይዘነጋም
አራኛው ዙር የሕዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በአዲስ አበባ ተጀመረ
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሀምሌ ግብጽ በሱዳን ጉዳይ ለመምከር በካይሮ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ባመሩበት ወቅት ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎችም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስምምነት ለመምጣት በተስማሙት መሰረት የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይታቸውን ካሳለፍነው ነሀሴ ጀምሮ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡
የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት በሶስቱ ሀገራት ዋና ከተሞች እንዲደረግ የተስማሙ ቢሆንም ሱዳን በገጠማት የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ውይይቱን ማስተናገድ አልቻለችም፡፡
የመጀመሪያው የሶስትዮሽ የባለሙያዎች ውይይት በግብጽ ካይሮ ሲካሄድ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ሶስተኛው ደግሞ ከአንድ ወር በፊት በካይሮ ተካሂዶም ነበር፡፡
አራተኛው ዙር የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ለአንድ ቀን ይቆያል የተባለው ይህ የሶትዮሽ ውይይት ከዚህ በፊት ወደ ስምምነት ባልተመጣባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያይ እና ወደ ስምምነት ሊመጣ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪው አባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጡ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሶስትዮሽ ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሶስትዮሽ ድርድር አለመቀጠል እና የግብጽ ተለዋዋጭ አቋም ማሳየት ለድርድሩ አለመሳካት ዋነኞቹ ምክንያቶች ነበሩ።
የሕዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ቀጣይ ድርድር መቼ እና የት ይካሄዳል?
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው የታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታው 91 በመቶ ደርሷል ተብሏል።
ኢትዮጵያዊያን በሚያዋጡት ገንዘብ እና በመንግስት ወጪ እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ 5ሺህ 200 ሜጋ ዋት ሀይል በማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ፕሮጀክት ነው።
የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 350 ሜጋ ዋት ሀይል ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሀይል በማመንጨት ላይ ይገኛል።
ግድቡ እስካሁን ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።