ተመራጩ ፕሬዝዳንት ባይደን እና ምክትላቸው ሀሪስ የብሔራዊ ደህንነት ም/ቤት አባላትን ይፋ አድርገዋል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትላቸው ካማላ ሀሪስ በትናንትናው ዕለት የብሔራዊ ደህንነት ም/ሜት አባላትን ይፋ አድርገዋል፡፡ በምክር ቤቱ ከተካተቱት መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዮሐንስ አብርሃም በቀዳሚነት ይገኙበታል፡፡
የብሔራዊ ምክር ቤቱ ዋነኛ ተግባር በብሔራዊ ደህንነት እና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ ፕሬዝዳንቱን ማማከር እንዲሁም እነዚህን ፖሊሲዎች በመንግሥት ተቋማት ማስተባበር ነው፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዮሐንስ አብርሃም የኋይት ሀውስ የብሔራዊ ደህንነት ም/ቤት ኃላፊ እና ዋና ጸኃፊ ሆነው ተሰይመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የባይደን-ሀሪስ ሽግግር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ዮሐንስ አብርሃም ፣ በባይደን ሀሪስ አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የፖሊሲ እና የአስተዳደር ጉዳዮች በመሪነት ለማማከር እና ለማስተባበር በመዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዮሐንስ በሃርቫርድ ኬኔዲ የመንግስት ትምህርት ቤት ፋኩልቲ በአስተዳደር (ማኔጅመንት) ዘርፍ በማስተማር ላይም ይገኛሉ፡፡ በኦባማ-ባይደን የአስተዳደር ዘመን ፣ አብርሃም የፕሬዚዳንቱ ምክትል ረዳት እና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ከፍተኛ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በኋይት ሀውስ የህዝብ ተሳትፎ እና የመንግስት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው የሠሩ በቤተመንግሥቱ ልምድ ያላቸው ግለሰብ ናቸው፡፡
ዮሐንስ የኢንቨስትመንት አማካሪ በሆነው በቫንጋርድ ግሩፕ ዓለም አቀፍ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ኩባንያ የአመራር ቡድን ውስጥ እንዲሁም በኦባማ ፋውንዴሽን ውስጥ ከፍተኛ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ በስፕሪንግፊልድ ቨርጂኒያ የተወለዱት ዮሐንስ አብርሀም ከያሌ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪ እና ከ ‹ሃርቫርድ ቢዝነስ› ትምህርት ቤት በከፍተኛ ማዕረግበቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን እና ምክትላቸው ሀሪስ ዮሐንስ አብርሃምን ጨምሮ 21 የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት አባላትን ይፋ ማድረጋቸውን የባይደን-ሀሪስ የሽግግር ክፍል አስታውቋል፡፡