ትራምፕ መሸነፋቸውን ያመኑት በኮፒቶል ሂል ቀስቅሰዋል የተባለውን አመጽ ተከትሎ በደረሰባቸው ውግዘት ነው ተብሏል
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 3 ቀን 2020 የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ “ተጭበርብሯል” በሚል ውንጀላ ሲያቀርቡ የነበሩት ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መሸነፋቸውን አመኑ፡፡
“ምርጫው ተጭበርብሯል” በሚል ውትወታ ላይ የነበሩት ትራምፕ በመጨረሻም ቢሆን የሥልጣን ሽግግሩ እንደሚካሄድ መግለጻቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ባለመመረጣቸው ብስጭት ውስጥ የቆዩት ትራምፕ ምርጫውን እርሳቸው እንዳሸነፉ ሲገልጹ መቆየታቸው ቢታወስም ትናንትና ግን 12 ቀናት በኋላ ማለትም ጥር 20 ቀን 2021 ከኋይት ሀውስ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ በአሜሪካ የካፒቶል ሂል የተካሄደው በጉልበት የታገዘ አመጽ አሰቃቂ ነበር ያሉት ትራምፕ በድርጊቱ እንደ ሁሉም አሜሪካውያን እርሳቸውም እንደተከፉና አንደተቆጡ ገልጸዋል፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ቢደን የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ባያስተላልፉም የስልጣን ሽግግር እየተደረገ እንደሆነና ይህም እንደሚቀጥል አምነዋል ፡፡
ከሰሞኑ በአሜሪካ የካፒቶል ሂል የተካሄደው በጉልበት የታገዘ አመጽ አሰቃቂ ነበር ያሉት ትራምፕ በድርጊቱ እንደ ሁሉም አሜሪካውያን እርሳቸውም እንደተከፉና አደንደተቆጡ ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱ በትራምፕ ደጋፊዎች እንደተደረገ የተገለጸ ሲሆን ዓለም ሁሉ ድርጊቱን በአሳፋሪነት ተመልክቶታል፡፡
ትራምፕ ከቤተ መንግስት ላለመውጣት ያቀናበሩት አመጽ ነው የተባለ ሲሆን ትራምፕ መሸነፋቸውን ማመን አለባቸው በሚል የሪፐብሊካን ሰዎች ጭምር በቁጣ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ትራምፕ ግን ብሔራዊ የጸጥታ ሀይልና የፌዴራል ሕግ አስከባሪ ኃይል እንዲላክ ማዘዛቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ከዚህ ሁሉ በኋላም ቢሆን ከ12 ቀናት በኋላ የኋይት ሀውስ አለቃ እንደማይሆኑ አምነዋል፡፡ ይህንን ያሉበት ንግግር በኋይት ሀውስ በቪዲዮ ተቀርጿል፡፡ ቪዲዮው እንዲቀረጽ ያደረጉት በርካታ ባለሥልጣናት ከሥልጣን እየለቀቁባቸውና እርሳቸውም እንዳይከሰሱ በመስጋት መሆኑን የኋይት ሀውስ አማካሪ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በተወያዩበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ አማካሪው የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ትራምፕ መከሰስም የማይቀር እንደሆነ መግለጻቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ጥር 20 ቀን 2021 አዲስ አስተዳደር ቦታውን እንደሚረከብ የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ዋና ትኩረታቸው የተረጋጋና ሥነ ስርዓቱን የጠበቀ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ማድረግ ነው ብለዋል፡፡