የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በይፋ ከኃላፊነት ለቀቁ
ዶ/ር ጌታቸው ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ ባለስልጣኑን በዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል
ዋና ዳይሬክተሩ ያቀረቡት የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት ማግኘቱን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) አቅርበውት የነበረው የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት አገኘ፡፡
ለጥያቄው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ናቸው ምላሽ የሰጡት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄውን ተቀብለው ማሰናበታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸውም ዶ/ር ጌታቸው በተለይ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ደብዳቤው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፈርሞ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ለዶ/ር ጌታቸው የደረሰ ሲሆን ከሳለፍነው መጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ ስንብቱ የተፈቀደላቸው መሆኑን ያትታል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህሩ ከመጋቢት 27 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ነበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሿሚነት ባለስልጣኑን በዋና ዳይሬክተርነት ያገለገሉት፡፡
ባለስልጣኑ የሚዲያ ዘርፉን ለማሻሻል ሲያደርግ የነበረውን ጥረትም ሲመሩና ሲያተባብሩ ነበር፡፡ ሆኖም ካሳለፍነው ወር የመጨረሻ ሳምንታት ጀምሮ ተቋሙን ለመልቀቅ ስለመጠየቃቸው ሲነገር ነበር፡፡
ሆኖም ከኃላፊነት ለመልቀቅ የፈለጉበትን ምክንያት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸውን ተክቶ ማን ተቋሙን ሊመራ እንደሚችል ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ከጽህፈት ቤታቸው የተገለጸ ነገር የለም፡፡
አቶ ወንድወሰን አንዷለም የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ይታወሳል፡፡