የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በእስር ላይ ስለሚገኙ ጋዜጠኞች ምን አለ?
“እኛ የምንወደው ጋዜጠኞች ባይታሰሩ ነው ምክንያቱም ነጻ ሆነው መስራት አለባቸው”
“የወላይታ ማህበረሰብ ሬዲዮ ስርጭት የተቋረጠው ከባለስልጣኑ እውቅና ውጭ ነው”- የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በእስር ላይ ስለሚገኙ ጋዜጠኞች ምን አለ?
በሰሞንኛው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ማህበር መግለጫ የተነሳውን የታሰሩ ጋዜጠኞችን ጉዳይ እንዴት ተመለከተው ሲል አል ዐይን አማርኛ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንን ጠይቋል፡፡
ማህበሩ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ለታሰሩ የአስራት ቴሌቪዥን እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኞች መንግስት አፋጣኝ ፍትህን ይስጥ ሲል መንግስትን የሚያሳስብ መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡
መግለጫውን በወቅቱ እንዳላዩት የገለጹልን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተርን ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) የመግለጫውን መውጣት አድንቀዋል፡፡
“መውጣቱ በጣም ጥሩ ነው እንደዚህ ዓይነት ማህበራት በአንድ ወገን ለሙያዊነትና ለሙያው መከበር ይሰራሉ ይሟገታሉ በሌላ ወገን ደግሞ ሙያተኞች ህግን አክብረው የዕለት ተዕለት ስራቸውን እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ የህግ ጫና እንዳይደርስባቸው ይሟገታሉ ይሄ በዋናነት የእነሱ ስራ ነው” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
መንግስት አፋጣኝ ፍትህን እንዲሰጣቸው በማህበሩ የተጠየቀላቸውን ጋዜጠኞች በተመለከተ ባለስልጣኑ በሩቅ ከሚሰማው ባሻገር ጉዳዩ በዋናነት የፍትህ አካሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“እኛ የምንወደው ጋዜጠኞች ባይታሰሩ ነው ምክንያቱም ነጻ ሆነው መስራት አለባቸው ሙያውም የሚያድገው የዛን ጊዜ ነው፡፡ ‘ስፔስ’ ያስፈልጋቸዋል ያን ‘ስፔስ’ ለመፍጠር ነው ይሄ ፖሊሲ (አዲሱ የሚዲያ ፖሊሲ) እና ፖሊሲውን ተከትለው የሚወጡትም ህጎች የሚሞክሩት” ሲሉም አስቀምጠዋል፡፡
ሆኖም ጋዜጠኞች ነጻ ሆነው ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የመፈለጉን ያህል ኃላፊነት እንዳለባቸውም ነው “ነጻ ሆኖ የሚሰራ ሚዲያ ስንል ነጻ ሆነው የሚሰሩ ጋዜጠኞች ማለት ነው” በሚል የሚገልጹት ዳይሬክተሩ የሚናገሩት፡፡
“ህግን አክብረው መረጃን የማግኘት መብታቸውን ተጠቅመው ስራቸውን እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ በምንም ዓይነት መልኩ ሊታሰሩ አይገባም፡፡ ነገር ግን ስራቸውን ከሰሩ በኋላ ተጠያቂ ናቸው፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ ይጠየቃሉ” ያሉም ሲሆን “አለበለዚያ ጋዜጠኝነት የወደድነውን ነገር ለመስራት ‘ላይሰንስ’ ሊሆን ነው ማለት ነው” በሚል ይናገራሉ ሙያዊ ተጠያቂነቱ ከሌለ ራሳቸውን ጋዜጠኞቹን “ለብልሽት” እንደሚዳርጋቸው በመግለጽ፡፡
ተጠያቂነቱ ሃሳብን ከማስተላለፍ ጋር ሊቆራኝ እንደማይገባም ዳይሬክተሩ ያነሳሉ፡፡ ሆኖም በህግ ጭምር የሚያስጠይቁ ነገሮች አሉ የሚሉም ሲሆን ‘ብሄርን ከብሄር ማጋጨት፣ ማነሳሳት’ በህግ ጭምር እንደሚያስጠይቅ እና የሚመለከታቸው አካላት በህጉ አንቀጾች ላይ ተመስርተው ክስን ቢመሰርቱ ጥፋት ሰሩ የሚያስብላቸው እንዳይደለም ይጠቁማሉ፡፡
በቅርቡ በዎላይታ ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የጸጥታ አካላት “ዎጌታ” ወደተሰኘው የአካባቢው ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ “ገብተው ስርጭቱን አስቁመዋል” መባሉን ተከትሎ የተለያዩ ሃሳብ አስተያየቶች ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበሩም “ተቀባይነት የሌለው ልምምድ” ሲል ነው በመግለጫው ያወገዘው፡፡
ባለስልጣኑ ድርጊቱን እንዴት እንደተመለከተው እና በወቅቱ የወሰዳቸው እርምጃዎች ካሉም በሚል አል ዐይን አማርኛ ጠይቋል፡፡
የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያውን ስርጭት በተመለከተ “በትክክል ማን ነው ያስቆመው የሚለውን ለመመለስ የሚችል አካል ያለ አይመስለኝም” የሚሉት ዳይሬክተሩ እዛው አካባቢ ያሉ ሰዎችን እጠይቃለሁ እስካሁን ምላሽ አላገኘሁም” ሲሉ መልሰዋል፤ ከሁኔታዎች መልስ ጣቢያው በአስቸኳይ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን በመጠቆም፡፡
“በእኛ በኩል አጣርተን የሚያስጠይቃቸው ይዘት ስለማሰራጨታቸው የደረስንበት ነገር ስለሌለ በዛ ፍጥነት ልንደርስ ስለማንችልም ማንም ይሁን ያስቆመው አካል ከእኛ እውቅና ውጪ ነው የተደረገው፡፡ በኋላ ግን ወዲያው የመቆሙ ጉዳይ ወደኛ እንደመጣ ሬዲዮ ጣቢያው ወደ መደበኛ ስራው እንዲመለስ ነው ያደረግነው” ብለዋልም፡፡
ሆኖም ድርጊቱ በሚመለከተው አካል ማለትም በባለስልጣኑ የተደረገ እንዳይደለም ገልጸዋል፡፡
ይህንንም “አንዳንድ ጊዜ እዛው አካባቢ ያሉ አስተዳደርና የጸጥታ አካላት ከሁኔታዎች ተነስተው የሚወስዱት ሊሆን ይችላል እንጂ እንዲህ ዓይነት ነገር ተመክሮበት ህግን ጠብቆ የሚመለከተው አካል ያደረገው ነገር አይደለም ሬዲዮ ጣቢያን የመዝጋት የመክፈትም ሆነ ፍቃድ የመስጠት ስልጣን የባለስልጣኑ ነው” በሚል ነው የሚያስረዱት፡፡
ባለስልጣኑ ከህግና የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራበት አግባብ ቢኖርም የወላይታውን በተመለከተ ግን የተሟላ መልስን ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡