ኬንያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን የድንበር ውዝግብ ጉዳይ ከሚመለከተው ዓለም አቀፍ የፍርድ ሂደት ራሷን አገለለች
ሀገራቱ የሚወዛገቡበት የባህር ላይ ድንበር 160 ሺ 580 ካሬ ኪ.ሜ ስፋት ያለው ሲሆን ትልቅ የነዳጅና ጋዝ ክምችት እንዳለው ይታመናል
ናይሮቢ ይህን ያደረገችው ፍርድ ቤቱን በገለልተኛነት በመክሰስ ነው
ኬንያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን የባህር ድንበር ይገባኛል ውዝግብ ጉዳይ ከያዘው ዓለም አቀፍ የፍርድ ሂደት ራሷን አገለለች፡፡
ናይሮቢ ዓለም አቀፉ የፍትህ ተቋም (ICJ) ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ያቀረበችውን የችሎት የቀጠሮ ጊዜ ይራዘምልኝ ጥያቄ አለመቀበሉን በመቃወም ‘ገለልተኛነት ይጎድለዋል’ በሚል ደጋግማ ስትከስ ነበር፡፡
በመሀኑም ተቋሙ ጉዳዩን ለማየት ለዛሬ ይዞት ከነበረው ቀጠሮ ራሷን ማግለሏን እና በቀጠሮው እንደማትገኝም ነው ያስታወቀችው፡፡
ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አፍሪካ የኬንያው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኪሃራ ካሪዩኪ ለ ‘ዘ ሰንዴይ ኔሽን’ ተናገሩ ብሎ እንደዘገበው ከሆነ፤ ኬንያ ውሳኔዋን ለተቋሙ አሳውቃለች፡፡
ኬንያ “ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ጥግ ይዟል” የሚል ክስም ታቀርባለች፡፡
ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት የሚቻኮልበት ምንም አጣዳፊ ምክንያት የለም ሲሉም ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ይናገራሉ፡፡
ስለሆነም “ከዛሬ ከመጋቢት 15 ቀን 2021 ጀምሮ፤ በችሎቱ እንደማንሳተፍ ለፍርድ ቤቱ ለማሳወቅ እንፈልጋለንም” ነው ኪሃራ ያሉት፡፡
ችሎቱ እንዲራዘም ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ መደረጉን የተቃወመችው ኬንያ ሶማሊያዊው አብዱል ቃዊ አህመድ ዩሱፍ ከፍርድ ቤቱ ዳኞች መካከል አንዱ መሆኑንም ትቃወማለች፡፡
ሁለቱ ሀገራት የሚወዛገቡበት እና በህንድ ውቅያኖስ ላይ የሚገኘው የባህር ላይ ድንበር 160 ሺ 580 ካሬ ኪ.ሜ ስፋት ያለው ሲሆን ትልቅ የነዳጅና ጋዝ ክምችት እንዳለው ይታመናል፡፡
አሳን በስፋት ለማስገር የሚያስችል ከፍተኛ ዐቅም እንዳለውም ነው የሚነገረው፡፡
የይገባኛል ጉዳዩን ሶማሊያ ነች እ.አ.አ 2014 ወደ አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የወሰደችው፡፡
ሶማሊያ፤ የባህር ላይ ወደቡ በተመሳሳይ አቅጣጫ ቀጥሎ ወደ ሀገሪቱ የደቡብ ምስራቅ አካባቢ እንዲሆን የምትሻ ሲሆን፤ ኬንያ በበኩሏ የባህር ላይ ወደቡ በተለይም በባህር ዳርቻ ያለው ወደብ ሁለቱም ሀገራት የሚጋሩት ነው በማለት ትሞግታለች፡፡
ሃገራቱ በተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮችም ይወዛገባሉ፡፡ ሶማሊያ ኬንያ የጁባ ላንድ ራስ ገዝ አስተዳደርን ትደግፋለች በሚል በጣልቃ ገብነት ትከሳለች፡፡
በቅርቡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማቋረጧን ማስታወቋም የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም ሀገራቱ አሁንም ቢሆን በጸረ-አልሻባብ ትግል በትብብር እየሰሩ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡