“ሮይተርስ ሌላ ዘጋቢ እንዲልክ ጠየቅን እንጂ ፍቃዱን አላገድንም”-ብሮድካስት ባለስልጣን
ከዘገባዎች ሚዛናዊነት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን እንደታርም ተደጋግሞ ቢነገራትም ለማረም አለመቻሏም ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው
ወኪል ዘጋቢው ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ተንቀሳቅሳ ልትሰራ የምትችልበት አግባብ እንደሌለም አስታውቋል
“ሮይተርስ ሌላ ዘጋቢ እንዲልክ ጠየቅን እንጂ ፍቃዱን አላገድንም”-ብሮድካስት ባለስልጣን
ሮይተርስ በኢትዮጵያ እንዳይሰራ አልከለከልኩም ሲል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ የኢትዮጵያ ወኪል ዘጋቢውን እንጂ የተቋሙን የዘገባ ስራዎች ፍቃድ አለመሰረዙንም አስታውቋል፡፡
“የሚመለከታቸውን አካላት አካቶ በሚዛናዊነት ከመስራት ይልቅ የአንድ ወገን መረጃዎችን ብቻ የመጠቀም ችግሮች እንዳሉ ለወኪል ዘጋቢዋ ደጋግመን ብናስታውቅም አላረመችም” ያሉት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም “ለተቋሙ በማሳወቅ የወኪል ዘጋቢነቷን ፈቃድ አገድን እንጂ ከሮይተርስ ጋር ያለን ግንኙነት አልተቋረጠም የዘገባ ፍቃዱንም አላገድንም”ሲሉ ለአል ዐይን አማርኘ ተናግረዋል፡፡
ከአሁን በኋላ “እንደ ወኪል ጋዜጠኛ ሆና ልትሰራ የምትችልበት” አግባብና እንቅስቃሴ እንደሌለ እና የሚሰጣት መረጃ እንደማይኖርም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ያስታወቁት፡፡
“ሮይተርስ ሌላ ጋዜጠኛ እንዲልክ ለዋና መስሪያ ቤቱ አሳውቀናል”ም ብለዋል አቶ ወንድወሰን፡፡
የቋሚ የሚዲያ ወኪል (ጋዜጠኛ) መታወቂያዋ በባለስልጣኑ መያዙንም አስታውቀዋል፡፡
እንድታርም ተደጋግሞ ስለተነገራት ነገር ምንነት አል ዐይን አማርኛ ላቀረበላቸው ጥያቄም “ምንም ዓይነት የኢንተርኔትም ሆነ የኮሙኒኬሽን ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ ከመቀሌ መረጃ አግኝተው ይሰራሉ ሲሰሩ ግን አዲስ አበባ ከሚገኘው የመንግስት አካል ‘ባላንስ’ አድርገው አይደለም ” አይደለም ሲሉ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
‘ባላንስ’ አለማድረጉ “ወደ አንድ አካል ጣት መቀሰር የአንድን አካል ፕሮፓጋንዳ ማራገብ” እንደሚሆንና ከጋዜጠኝነት ሙያ መርሆዎች እንደሚያፈነግጥም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
ባለስልጣኑ ይህን ጨምሮ የብሮድካስት አዋጁን ጨምሮ ሌሎች ህጎች ሲጣሱ የመቆጣጠር እና እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
አሁንም መቆጣጠሩን እንደሚቀጥል እና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ሌሎች የውጭ ሃገራት ብዙሃን መገናኛ ወኪል ዘጋቢዎችን ማነጋገሩንም ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣኑ ለሃገር ውስጥም ሆነ ለውጭ የሚዲያ ተቋማት ወኪል ዘገባዎች ፈቃድ ሰጪ አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡