ኢዜማ ላቀረባቸው አቤቱታዎች ምላሽ ካልተሰጠው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስድ እንደሚችል አስታወቀ
የብዙ ፓርቲዎች ውህድ የሆነው ኢዜማ “ዴሞክራሲያዊ ትግሌን እቀጥላለሁ” ብሏል
“ፓርቲው ድምጻችሁን ለኢዜማ የሰጣችሁትን ከልብ እያመሰገንን ያልመረጣችሁኝንም ውሳኔያችሁን አከብራለሁ” ብሏል
ኢዜማ በቅድመ ምርጫ እና በምርጫው ዕለት ላቀረባቸው አቤቱታዎች ምላሽ ካልተሰጠው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስድ እንደሚችል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በምርጫው ሂደት እና በቀጣይ ስራዎቹ ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።
ፓርቲው እንዳስታወቀው ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሂደቱ እና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ የተገለፀ ባይሆንም በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ ነበር።
“ቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትንና በየሰዓቱ ለምርጫ ቦርድ ያሳወቅናቸው በርካታ ችግሮችን ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካላት ይዘን የምንሔሄድበትን ሁኔታ ቀድመን ለሕዝብ የምናሳውቅ ይሆናል” ብሏል።
“በዘውግና በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የአገራችን የፖለቲካ ትርክት ላለፉት 30 ዓመታት ከአንድነት ይልቅ ልዩነቶቻችንን አግዝፎ በትውልዱ ላይ ቁርሾን ዘርቷል” ያለው ኢዜማ ዛሬም ከዚህ የማንነት የፖለቲካ አዙሪት መላቀቅ አለመቻሉን አክሏል።
“ላለፉት 30 ዓመታት እስከ 6ኛው ዙር ምርጫ ድረስ በምርጫ ብቻ ሥልጣን ለመያዝ የተሞከረው ሒደት ተስፋ ሰጪ ባይሆንም ዜጎች የምርጫ ተሳትፎ ማድረጋቸው አንድ ጥሩ እርምጃ ነው” ብሏል ፓርቲው።
ለዚህ ምርጫ ሰላማዊነትና የአገሪቱን የነገን ቀጣይነት በምርጫ ለማረጋገጥ፣ ዜጎች በምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ኢዜማ የበኩሉን ድርሻ በኃላፊነት ተወጥቷል የሚል የፀና እምነት እንዳለውም ገልጽል።
ኢዜማ ከምንም በላይ ለአገር መረጋጋትና ለሕዝብ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነትም በተግባር ማስመስከሩነም ገልጿል።
የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ ትግል ቀጣይነት ያለውና ከምርጫ በኋላም ቢሆን ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ ኢዜማ ጊዜያዊ ፓርቲ ሳይሆን ገና ከመነሻው ከምርጫ ወረዳ ጀምሮ ሲዋቀር ሩቅ ተጓዥና ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ነው ብሏል።
“ከዚህ አንጻር በምርጫው ሒደት ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በሕግ አግባብ እየጠየቅን ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የድርጅቱን መዋቅር ይበልጥ በማጠናከር ወደ ሥራ መግባቱን” ገልጿል።
“ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቷና የሕዝቧ ደህንነት ተጠብቆ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሳት ጠንካራ አገር እንድትሆን ኢዜማ ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ሆኖ በጥንካሬ እቀጥላለሁ” ያለው ፓርቲው፤ “ድምጻችሁን ለኢዜማ የሰጣችሁትን ከልብ እያመሰገንን ያልመረጣችሁንንም ውሳኔያችሁን አከብራለሁ” ብሏል።