ከቁሳቁስ እጥረት ጋር በተያያዘ ምርጫው የተቋረጠባቸው ቦታዎች አሉ- ምርጫ ቦርድ
ከምርጫው ጋር በተያያዘ ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠመም ቦርዱ አስታውቋል
ህዝቡ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ምርጫውን በማከናወኑ ቦርዱ ምስጋናውን አቅርቧል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን እታውቀዋል።
“ከምርጫው ጋር በተያያዘ ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ችግር አላጋጠመንም” ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን፤ አማራ ክልል አንድ ጣቢያ ላይ ሰዎች ሰዎች እርስ በእስር ተጋጭተው ምርጫው ተቋርቶ ነበረ፤ በዚያው ክልል አንድ ጣቢያ ላይ የአስተዳደር አካላት ገብተው አንወጣም በማለታቸው የቦርዱ አስፈጻሚ ለቆ ወጥቶ እንደነበረም አስታውቀዋል።
“ሆኖም ግን የምርጫው ሰላማዊነት በጣም በመልካም ሁኔታ ተጠናቋል፤ የከፋ የፀጥታ ችግር አልገጠመንም” ብለዋል።
ኦሮሚያ ክልል አንድ አንድ የምርጫ ክልል ችግር አለባቸው ተብለው በተለዩ አካባቢዎች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከስጋት የተነሳ ያልተከፈቱ እንደነበሩም አስታውቀዋል።
በዚህም በምስራቅ ሀረርጌ፤ የተወሰኑ ጣቢያዎች ያልተከፈቱ እንደነበሩ እና ምእራብ ሸዋ ናኖ በሁለት ጣቢያዎች ላይ ታጣቂዎች የምርጫ ሂደቱን ለመረበሽ ሞክረው እንደነበረም አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ ላይ አጋጥሞ ከነበረ የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት ጋር በተያያዘ፤ ችግሩ የተከሰተው ከማሸጊያ ጋር ተያይዞ ነው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ቀኑን ሙሉ ተሰርቷል ብለዋል።
በሲዳማ በ18 የምርጫ ክልሎች የምርጫ የቁሳቁስ እጥረት ማጋጠሙን አስታውሰው፤ ቦርዱ በ1162 የምርጫ አዋጁ መሰረት ምርጫው እንዲቋረጥ ማደረጉን አስታውቀዋል።
ቁሳቁስ ከተሰራጨ በኋላ ነገ ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ በሲዳማ የምርጫ ክልሎች በሙሉ ድምጽ የመስጠት ሂደቱ ይቀጥላል ብለዋል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በጋምቤላም በተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች በድምጽ መስጫ እጥረት ምክንያት ምርጫው ተቋርጧል፤ ነገ የምርጫ ቁሳቁስ ከደረሰ በኋላ መቼ እንደሚቀጥል እንደሚወሰንም ገልጸዋል።
ቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አክለውም በምርጫ ጣቢያዎች ላይ ችግሮች እና ውስንነቶች መስተዋላቸውን በመጥቀስ ይቅርታ ጠይቀዋል።
አማራ እና ደቡብ ላይ ቅሬታዎች እንደነበሩም የገለጹ ሲሆን፤ በአንድ አንድ የመርጫ ጣቢያዎች ላይ መሻሻሎች ተስተውለዋል ብለዋል።
ህዝቡ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለመረጠው ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብም ምስጋና አቅርበዋል።