“የምርጫው የእስካሁን ሂደት መልካም ነው” - የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን
ታዛቢ ቡድኑ በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 21/22 ምርጫ ጣቢያ 4 እና 5 የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በአካል ተገኝቶ ታዝቧል
“መራጩ ከንጋት 12፡00 ጀምሮ ድምጽ መስጠት መጀመሩንም ተረድቻለሁ”ም ብለዋል ታዛቢ ቡድኑ
የምርጫው የእስካሁን ሂደት በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ገለጹ።
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ዛሬ ረፋዱ ላይ በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 21/22 ምርጫ ጣቢያ 4 እና 5 የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በአካል ተገኝቶ ታዝቧል።
የቡድኑ መሪ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ “ቡድኑ ከገባበት ቀን ጀምሮ የምርጫ ሂደቱን በተለያየ መልኩ ሲከታተል ነበር” ብለዋል።
የምርጫ ዝግጅቱን በተመለከተ አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው ሠፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከጸጥታ ተቋማት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሌሎች አካላት ጋር የምርጫውን ዝግጅት በተመለከተ መወያየታቸውንም አስታውሰዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ የጸጥታና የሎጅስቲክስ ችግሮች ቢስተዋሉም የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ይህንን ተቋቁመው ምርጫውን ማስፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
የምርጫው የእስካሁን ሂደትና የዛሬ ድምጽ አሰጣጥ በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት የቡድኑ መሪ።
ቡድኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ የክልል የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱን ተዘዋውሮ መመልከቱን ጠቁመው፤ “የእስስካሁኑ ሂደት ጥሩ ደረጃ ላይ ነው” ብለዋል።
መራጩ ህዝብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ በመረዳትና በመተግበር ምርጫው ቅደም ተከተላዊ ሥነ-ሥርዓቱን በተከተለ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል ኦባሳንጆ።
“መራጩ ከንጋት 12፡00 ጀምሮ ድምጽ መስጠት መጀመሩንም ተረድቻለው”ም ብለዋል።
በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ማነጋገራቸውን ገልጸው፤ እስካሁን ቅሬታ ያቀረበ ፓርቲ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
ከዚህ በኋላም በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር የምርጫ ሂደቱን እንደሚታዘብ የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መግለፁን ኢዜአ ዘግቧል።