መንግስት በዩኤስኤይድ ጉዳይ የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጠየቀ
ኢትዮጵያ በዓመት በዩኤስአይድ በኩል ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ስታገኝ ነበር
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር በዩኤስኤይድ ላይ ያሳለፉት ውሳኔ ድንገተኛ መሆኑ በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ድርጅቶችን ስራ እንደጎዳ ምክር ቤቱ አስታውቋል
መንግስት በዩኤስኤይድ ጉዳይ የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡
ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ስልጣን የመጡት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የረድኤት ድርጅት ወይም ዩኤስኤይድ ከአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታዎች ውጪ ሌሎች ስራዎቹን እንዳይሰራ ማገዳቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ከድርጅቱ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ከዩኤስኤድ ጋር ሲሰሩ እንደነበር እና ውሳኔው ከባድ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ከ5 ሺህ በላይ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በአባልነት የያዘው የዚህ የምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን ለአል ዐይን እንዳሉት በዩኤስኤይድ ላይ የተላለፈው የ90 ቀናት ውሳኔ ከምንም በላይ ድንገተኛ መሆኑ ጉዳቱን የከፋ እንደዳደረገው ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ከሆነ በርካታ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች እየሰሯቸው የነበሩ እና ሊሰሯቸው ያቀዷቸው የሰላም፣ ጤና፣ ማህበራዊ እና ሌሎችም ስራዎች በውሳኔው ምክንያትን አስተጓጉሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እስከ 150 ሰራተኞች የነበሯቸው እና ከዩኤስኤይድ የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኙ የነበሩ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን አሰናብተዋል የሚሉት አቶ አህመድ ውሳኔው ተጀምረው የነበሩ በርካታ ስራዎች ማስቆሙን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው የመመለስ፣ የጤና አገልግሎቶች፣ የግጭት አፈታት ውይይቶች እና ሌሎች ስራዎች በዩኤስኤይድ ላይ በተላለፈው እገዳ ምክንያት ሊስተጓጎሉ እንደሚችሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
አቶ አህመድ አክለውም እንደ አገር በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አማካኝነት ሊፈጸሙ ይችላሉ ተብለው መንግስት የበጀት እና ሌሎች ዝግጅቶችን ባለማድረጉ ጉዳቱ ትልቅ ነውም ብለዋል፡፡
“የበጀት መቋረጡን እንደ እድል ልንጠቀምበት የሚገባም ነገር እንዳለ እንረዳለን፡፡ ሁሌ በሰው ሀገር በጀት መመስረት አንዱ ጉዳት ይህ ነው፡፡ ከፈተና ጋር የመጣ እድል ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን” ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
በዩኤስኤይድ ላይ የተላለፈው የ90 ቀናት እገዳ ይነሳል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄም “ከዚያ ፊትም ማስተካከያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እናምናለን፡፡ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ሳይቀር የተቃወማቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ የበጀት ድጋፉን ሙሉ ለሙሉ ይቋረጣል ወይም እንደበፊቱ በተለመደው መልኩ ሊቀጥል ይችላል ብዬም አላስብም፡፡ የበጀት ድጋፉ መቀነሱ ግን እሚቀር አይመስልም፣ አብዝቶ ማቀድ ከእኛ የሚጠበቅ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል አቶ አህመድ፡፡
ጉዳዩ መንግስት የዲፕሎማሲ እና ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርግ እንፈልጋለን ያሉት አቶ አህመድ እገዳው በግጭት ውስጥ ባለሀገር የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ቢያንስ ድጋፉ እንዲቀጥል የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጤና ሚኒስቴር ከአሜሪካ መንግሥት በሲዲሲ (CDC) ወይም ዩኤስኤይድ (USAID) አማካኝነት በተገኘ የበጀት ድጋፍ የሚከናወን ማንኛውም ስራም ሆነ ክፍያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከጃንዋሪ 24 2025 ጀምሮ እንዲቋረጥ ማሳሰቢያ እንደደረሰው ገልጿል።
ከአራት ዓመት በፊት በነበረው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ዘመን ኢትዮጵያ ከዋሸንግተን የምታገኛቸው የጤና ስራዎች ድጋፍ በጀት ከቀነሰባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች፡፡
እንደ አሜሪካ የውጭ እርዳታ ተቋም 2023 መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ በዓመት በዩኤስአይድ በኩል ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አግኝታለች፡፡
ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በበኩሉ ዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ንብረት እንዳይሸጡ እና እንዳይለውጡ አስጠንቅቋል፡፡
ባለስልጣኑ ባወጣው መግለጫ ከእኔ እውቅ እና ፍቃድ ውጭ ንብረት ማስተላለፍ፣ ማስወገድ ወይም መሸጥ ወይም ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ እንደማይችሉ ክልከላ ተጥሎባቸዋልም ብሏል።
ማሳሰቢያውን ተላልፈው በሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል፡፡
በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ አዋጅ መሰረት የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች በማንኛውም ምክንያት ስራቸውን ካቆሙ ንብረቶቻቸውን ለመንግስት እንዲያስረክቡ ያስገድዳል፡፡