በኦሮሚያ ክልል በእስር ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሰራተኞች ተለቀቁ
የክልሉ ፖሊስ ለምን የምርት ገበያ ሰራተኞችን እንዳሰረ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም
ሰራተኞቹ ከእስር ቢለቀቁም መጋዝኖቹ አሁንም እንደታሸጉ ናቸው ተብሏል
በኦሮሚያ ክልል በእስር ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሰራተኞች መለቀቃቸው ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኦሮሚያ ክልል ያሉት ሰባት ቅርንጫፎቹ ከሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮመዘጋታቸውን እና ሰራተኞቹ መታሰራቸውን መግለጹ ይታወሳል።
የምርት ገበያው ገበያው የኮርፖሬት ኮሙንኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ነጻነት ተስፋዬ ለአል ዐይን አማርኛ ከአንድ ሳምንት በፊት “በጊንቢ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ በደሌ፣ ቡሌሆራ፣ ነቀምት እና መቱ ያሉ የምርት ገበያ ማዕከሎች ከሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ፖሊስ መታሸጋቸውን ገልጸው ነበር።
እንዲሁም የክልሉ ፖሊስ የምርት ገበያው መጋዝኖች ይሰሩ የነበሩ “58 አመራሮች እና ሰራተኞች በእስር ላይ ናቸው” ማለታቸውም ይታወሳል።
እነዚህ የምርት ገበያው ሰራተኞች ካሳለፍነው ቅዳሜ ማለትም ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከእስር መለቀቃቸውን አቶ ነጻነት ነግረውናል።
ይሁንና በኦሮሚያ ክልል ያሉ እና በክልሉ ፖሊስ ታሽገው የነበሩ መጋዝኖች አለመከፈታቸውን ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እስካሁን ድረስ የምርት ገበያውን መጋዝኖች እንዳሸገ እና ሰራተኞቹንም ለምን እንዳሰረ እንዳላሳወቃቸው አቶ ነጻነት ገልጸዋል።
ከ14 ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአገር አቀፍ ደረጃ 25 የግብርና ምርቶች ናሙና መቀበያ እና ምርት መቀበያዎች ማዕከሎች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ሰባቱ በኦሮሚያ ክልል ይገኛሉ።
የምርት ገበያው መጋዝኖች መታሸግ እና ከስራ ውጪ መሆን አምራች አርሶ አደሮች፣ ምርት ላኪዎች ምርቶቻቸውን ለተቋሙ አቅርበው ወደ ውጪ እንዳይላክ በማድረጉ ሀገሪቱ ገቢ እንድታጣ እያደረገ መሆኑንም አቶ ነጻነት ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አስቀድመው ምርት ወደ መጋዝኖቹ የላኩ አርሶ አደሮች እና ምርት ላኪዎች ምርታቸው መጠኑ ሊቀንስ አልያም ሌላ ያልተገመቱ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉም አቶ ነጻነት ገልጸዋል።
የውጪ ንግድን ለማበረታታት ሲባል በተለይም ቡናን ወደ ውጪ መላክ የሚችሉት የኢትዮጵያ ምርት ገበያውን ጨምሮ ህብረት ስራ ማህበራት እና ቡና ላኪ ኩባያዎች ቡናን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ላይ መሆናቸውን ሰምተናል።