በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ምን ምን ናቸውʔ
በ2015 በኢትዮጵያ ላይ ከ6 ሺ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል ተባለ
4ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር በመከበር ላይ ይገኛል
በጥቅምት ወር በሙሉ የሚከበረው 4ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር በአዲስ አበባ በመከበር ላይ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብረሃም በላይ፤ የሳይበር ወንጀሎች የሀገራት ዋነኛ የደህንነት እና የህልውና ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።
ዶ/ር አብረሃም በንግግራቸው አክለውም፤ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ቴክኖሎጂን እንደምናስፋፋ ሁሉ፤ የሳይበር ደህንነት ላይ እኩል መስራት ይገባናል ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃም ይሁን እንደ ዓለም የሚደረጉ የሳይበር ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።
በተለይም በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።
ሳይበር በባህሪው ድንበር የለሽ፣ ውስብስብ እና ኢ-ተገማች በመሆኑ አንድ ሀገር የሳይበር ደህንነት አቅሙን ካላሳደገ ሀገራዊ ሉዓላዊነቱ እና ብሄራዊ ጥቅሙ ከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃልም ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትጵያ የሳይበር ምህዳሩን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ በግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ጨምሮ በሀገራችን ቁልፍ የመንግስት መሰረተ-ልማቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች የብሄራዊ ደህንነት ስጋት መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ሶካ ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢትዮጵያን ቁልፍ ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ-ልማት ደህንነትን በማረጋገጥ ለሀገሪቱ የሰላም፣ የልማት እና የዲሞክራሲ መርሃ ግብሮች ማስፈፀሚያ እንዲሆኑ የማድረግ እና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሞች የማስጠበቅ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
በኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓመት 2015 ዓ/ም 6 ሺ 959 የሳይበር ጥቶች መፈጸማቸው ተነግሯል።
ከሳይበር ጥቃቶቹ ውስጥም 2 ሺ 559 ያህሉ በድረ ገጽ ላይ የተፈጸሙ ሲሆኑ፤ 1 ሺህ 295 ያህሉ ደግሞ የማልዌርና የፒሺግ መሆናቸው ተጠቁሟል።
እንዲሁም 603 በመሰረተ ልማት ቅኝት፣ 1 ሺህ 493 መሰረት ልማት የማቋረጥ (አብዛኛው የፋይናንስ ተቋማትን ኢላማ ያደረገ)፣ 695 ሰርጎ የመግት ሙከራ እና 145 ሌሎች የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል።
የሳይበር ጥቃቶቹ የፋይናንስ እና የፀጥታ ተቋማትን፣ እንደ ቴሌኮምና መብራት ያሉ ቁልፍ ተቋማት መሰረተ ልማቶችንና ቁልፍ የመንግስት ተቋማትን ኢላማ ያደረጉ ነበሩ ተብሏል።
በ2015 የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን መከላከል በመቻሉም በሀገር ላይ ሊደርስ የነበረ 23.2 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉን የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ አስታውቀዋል።