ህወሓት በኬንያ ለሚደረገው“ድርድር” የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን አስታወቋል
የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለመደራደር መዘጋጀቱን የድርድር ቡድኑ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ አስታወቁ፡፡
የድርድር ቡድኑ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሌላኛው የድርድር ቡድኑ አባልና ከፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር በመሆን ከተለያዩ አካላት ጋር ንግግር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋንና ዶ/ር ጌዲዮን ቲሞቲዮስ፤ ከተባበሩት መንግስታት፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን እና ብሪታኒያ አምባሳደሮች ጋር መወያየታቸው አስታውቀዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን መንግስት ከህወሓት ጋር በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸውን አንስተዋል፡፡ የሰላም ንግግሩ መመራት ያለበት በተጀመረው የአፍሪካ ህብረት በኩል እንደሆነና ድርድሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መጀመር እንደሚችልም መግለጻቸውንም አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገልጸዋል፡፡
ከህወሓት ጋር የሚደራደረውና ከወር በፊት የተዋቀረው “ሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ” ከ15 ቀናት በፊት በይፋ ስራ መጀመሩን እንደገለጸ ይታወሳል።
ኮሚቴው ባካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባው በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚካሄደው የሰላም ውይይት የራሱን የአሰራርና ሥነምግባር አካሄድ ተወያይቶ መወሰኑንም አምባሳደር ሬድዋን በወቅቱ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚቴው በስሩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በመደራጃትም ኃላፊነት ተከፋፍሎ ስራውን መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር የሰላም አማራጮች እንዲታዩ እና የፌደራል መንግስቱን ወክለው በሰላም ውይይቱ ላይ የሚሳተፉ አባላት መመደባቸው ይታወሳል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ቡድኑ ሰባት አባላትን በውስጡ የያዘ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከወር በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙን መግለፃቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ፤ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እየተያደረጉ ነውም ብለዋል።
ህወሓት በበኩሉ በኬንያ መንግስት በተጠራው ድርድር የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን በሊቀ መንበሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ማስታወቁ ይታወሳል።