የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ ዴቪድ ሺን ስለ “ድርድር” ምን አሉ?
አምባሳደሩ ”በድርድሩ” ማዕከላዊው መንግስት ህወሐትን በአሸባሪነት መፈረጁን ለማንሳት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል ብለዋል
ዴቪድ ሺን “የትግራይ ኃይሎች የወደፊት እጣ ፋንታ” አስቸጋሪ ከሚሆኑ የድርድር ነጥቦች መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት የተለያዩ አሳዛኝ ክስተቶች እያስተናገደና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዋና አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ የጦርነቱ ተዋናዮች ማለትም የፌዴራል መንግስት እና ህወሐት ወደ የድርድር ሃሳብ መምጣታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
በፌዴራል መንግስት እና ህወሐት መካከል ያለውን ቀውስ በሰለማዊ መንገድ የሚፈታበት መንገድ ካለ፤ አሳዘኝ ውድመት ያስከተለውንና በርካቶችን ለሞትና እንግልት የዳራገውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
- ህወሓት በኬንያ ለሚደረገው“ድርድር” የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን አስታወቀ
- ከህወሓት ጋር ለሚደረገው ድርድር በፌዴራል መንግስት የተደራዳሪ ቡድን ተሰየመ
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ “ድርድር” ምን አሉ?
ህወሐት በኬንያ መንግስት አሸማጋይነት በናይሮቢ የሚደረግ የሰላም ንግግር ካለ በድርድሩ የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የፌዴራል መንግስት በበኩሉ የሀገር ብሄራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄድ ድርድር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑ በጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት አማካኝነት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ሁለቱም አካላት ለድርድር ዝግጁ ነን ቢሉም፤ በሁለቱም በኩል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ድርድሩን ያደነቅፉታል የሚል ስጋት አለ፡፡
አል ዐይን አማርኛ ቀደም ባሉ አመታት የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ ሆነው ላገለገሉት እና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚከታተሉት ዲፕሎማት አምባሳደር ዴቪድ ሽን ድርድርን የተመለከተ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
አምባሳደሩ ለአል ዐይን አማርኛ በኢ-ሜይል በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ”መደራደር ለኢትዮጵያውያን ከባድ ነው፤ ሁለቱም ስምምነት ለማድረግ በሚያስችል ስሜት ውስጥ አይደሉም፡፡ ነገርግን በትግራይ ያለው ግጭት ሁለቱንም በሚጎዳበት ደረጃ ደርሷል፡፡“
የፌደራል መንግስትና ህወሓት በድርድረ ሊስማሙ ይችሉበቸዋል ያሏቸውን ነጥቦች አስቀምጠዋል አምባሳደሩ፡፡
“ትግራይ የፌደራል መንግስት ህግጋትን ለመከተል እስከተስማማች ድረስ፤ ማዕከላዊው መንግስት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሐት) ከአሸባሪነት ሊሰርዝና ትግራይ ክልልን በመልካም አቋም በመያዝ የፌዴሬሽኑ አባል አድርጎ ለመቀበል ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል፡፡”
ማዕከላዊ መንግስት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቁጥጥር በትግራይ ክልል አዲስ የአካባቢ ምርጫ ለማካሄድ ሊስማማ ይችላል ሲሉም አክለዋል፡፡
አምባሳደር ዴቪድ ሺን የማዕከላዊ መንግስት ወታደሮች ወደ ትግራይ ክልል እስካልገቡ ድረስ፤ የትግራይ ኃይሎች ከትግራይ ውጭ ከሚሰነዝሩት ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ለመታቀብ ሊስማሙ ይችላሉም ብለዋል።
“በአማራ ታጣቂዎች፣ በማዕከላዊ መንግስት ሃይሎች እና ምናልባትም በአንዳንድ የኤርትራ ሃይሎች የተያዘው የምዕራብ ትግራይ የቀጣይ ድርድር ቀጣይ ጉዳይ እንደሚሆን ሁለቱም ወገኖች ሊስማሙ ይችላሉ” ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
አምባሳደር ዴቪድ ሺን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ለማጣራት ሁለቱም ወገኖች ሊስማሙ እንዲችሉም ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ዴቪድ ሺን ፌዴራል መንግስት እና ህወሐት ከስምምነት ላይ እንዳይደርሱ የሚያደናቅፍ ነጥብ ምን ሊሆን ይችላል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፤ እያንዳንዱ ነጥብ ተያያዥነት ያለው ቢሆንም“የትግራይ ኃይሎችን እጣፈንታ ጉዳይ” ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል፡፡
አምባሳደሩ“የትግራይ መከላከያ ሰራዊት (እና ሌሎች የማዕከላዊ መንግስትን የሚቃወሙ የክልል ወታደራዊ ሃይሎች) የወደፊት እጣ ፈንታ በጣም አስቸጋሪ ከሚሆኑ የድርድር ነጥቦች መካከል አንዱ ይሆናል”ም ብለዋል፡፡
በትግራይ እና በመላው ኢትዮጵያ የአካባቢ ሃይሎች በተበራከቱበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ሰላም ይመጣል ብሎ ማሰብ እንደሚያስቸግር የገለጹት አምባሳደር ዴቪድ ሺን፤መንግስት የትግራይን ጨምሮ ሁሉንም በእኩልነት ለማስተናገድ ዋስትና የሚሰጥ ስርዓት በመዘርጋት ሁሉም ሃይሎች የማዕከላዊ መንግስት ወታደራዊ ሃይል አካል የሚሆኑበት ማእቀፍ ማበጀት ይጠበቅበታል የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በማዕከላዊ መንግስት እና በትግራይ ክልል መካከል ስምምነት ላይ መድረስ አስፈላጊ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የትግራይ ጉዳይ በሚኬድበት ልክ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እየታዩ ያሉ የመገንጠል ዝንባሌዎችን ለማስቆምም የማዕከላዊው መንግስት ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ቀውስ ኤርትራ ስለተጫወተቸው ሚናና ቀጣይ መፍትሄዎች በተመለከተ በሰጡት ምላሽም ፤ የኤርትራ ሚና አሉታዊ እንደመሆኑ መፍትሄዎች ሊበጁለት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
“ኤርትራ በኢትዮጵያ ከፍተኛ አሉታዊ ሚና ተጫውታለች፤ ሁሉም" የኤርትራ ወታደሮችበአስቸኳይ ኢትዮጵያን ለቀው መውጣት አለባቸው እንዲሁም ማእከላዊው መንግስት እንዲመለሱ መፍቀድ ለበትም” ብለዋል አምባሳደሩ።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጥረት ማድረግ ያለባቸው መደበኛ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነታቸውን ለማዳበር መሆን አለበትም ብለዋል አምባሳደር ዴቪድ ሺን፡፡
አምባሳደሩ ይካሄዳል በሚባለው ድርድር የአሜሪካ ፍላጎት ምን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ፍላጎት ጦርነቱን በዘላቂነት እንዲያቆም፣ ወደ ትግራይ ክልል እና ወደ ማንኛውም ሌላ የተቸገረ አከባቢ ሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖር፣ የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መወገድ እና ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሁሉ ተጠያቂነት ማስፈን ነው። የአውሮፓ ህብረትም ተመሳሳይ ዓላማ አለው ብዬ አምናለሁ።
አሜሪካ እነዚህን ሁሉንም ወይም አብዛኛዎቹን ግቦች የሚያሳካ ማንኛውንም አፍሪካ መር አደራዳሪነት የምትደግፍ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ያም ሆኖ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚካሄደው ድርድር በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑ በአሜሪካ በኩል “ደስተኛ” ያለመሆን ነገር እንዳለ ግን አልሸሸጉም አምባሳደሩ፡፡
“አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት እንደምትቀበል ያለማቋረጥ ስትናገር የቆየች ቢሆንም፤ አንዳንድ ጊዜ በአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም ሂደት አዝጋሚ መሻሻል ሳትበሳጭ አልቀረችም፣ነገር ግን ያንን ሂደት ለመደገፍ ያለትን ዝግጁነት ቀጥላበታለች”ብለዋል አምባሳደር ዴቪድ ሺን።